ሰርከስ እያበረከተ ካለው አስተዋዕኦ አኳያ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነው

113
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 ሰርከስ ለሀገሪቷ እያበረከተ ካለው አስተዋዕኦ አንጻር የሚሰጠው ትኩርት አናሳ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገለጹ። ''ሰላም ኢትዮጵያ’’ በተሰኝ ድርጅት የኢትዮጵያ ሰርከስ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና እድሎች በሚል መሪ ሀሳብ ተመክሯል። በውይይቱም በኢትዮጵያ የሰርከስ ስፖርት ከተጀመረ 25 ዓመታት ያህል እድሜ እንዳለው ነው የተነገረው። ። በእነዚህ ዓመታትም ኢትዮጵያ የሰርከስ አርቲስቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ስራዎቻቸውን በማቅርብ የሜዳሊያ ሽልማት ከማምጣት ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ድርጅቶችን መቀላቀል ችለዋል ተብሏል። ለአብነትም በተለያዩ ሀገራት ስራዎቹን በማቅረብ በሚታወቀውና መቀመጫውን ካናዳ ባደረገው በስመ ገናናው ሰርከስ ዲሰሌ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሰርከስ አርቲስቶች ኮንትራት ተሰጥቷቸው በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየዞሩ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ኢትዮጵያዊያን የሰርከስ ትርኢት አቅራቢዎች ባለቸው አቅምም የብዙዎችን ቀልብ መሳብ በመቻላቸው ከዓመት በፊትም ኢትዮጵያዊያን የሰርከስ ትርኢት ባለሙያዎች ሊትል ቢግ ሹት የተሰኝ የአሜሪካ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ተጋብዘው ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ከፍተኛ አድናቆትም አትርፈዋል። ይህም እንደ ሀገር የሰርከስ ባለሙያዎችን በገንዘብ ደረጃ እራሳቸውና ቤተሰቦቻቸውን ከመጥቀም ባለፈ  የውጭ ምንዛሬንም እያስገኙ እንደሆነ ተወስቷል። ይሁን እንጅ እንደ ሀገር ሰርከስ ትኩረት እንዳልተሰጠውና በመንግስት በኩልም የሚሰጠው ትኩርት አናሳ መሆኑ ነው የሚነገረው። የሰርከስ አርቲስት ባለሙያዎችም ይህን ችግር በመፍታት የሰርከስ ኢንዱስትሪው እንደ ሀገር  የሚያበረከትውን ውጤት በመጠቀም በትኩረት መሰራት ይገባል ይላሉ። የኢትዮ-ሰርከስ ባለቤት አቶ ክብሮም በርሄ ኢንዱስትሪው የሀገርን ስም በማስጠራት በኩል ብዙ አስትዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል። በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት፣ የስራ እድል በመፍጠርና ከሱስ የጸዳ ወጣት በማፍራት ሰፊ ሚና በሚያበረክተው ልክ እውቅና እንዳልተሰጠው ነው የተናገሩት። የሰርከስ ባህርዳር መስራች ወይዘሪት ውዴ ዘለቀ በበኩሏ በሙያው እየሰሩ የኢትዮጵያን ስም ለሚያስጠሩ ባለሙያዎች የሚሰጠው ድጋፍም ሆነ ማበረታቻ የለም። በኢትዮጵያ ከተጀመረ አንስቶ በመንግስት በኩልና በፖሊሲ ደረጃ ድጋፍ እንደሌለውም ነው የተነገረው። ይህም የሰርከስ ኢንዱስሪው ላይ ላይ ጫና እየፈጠረ ነውም ብላለች። በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጽጌ እስካሁን ለሰርከስ የተሰጠው ትኩርት አናሳ አልካዱ። አቶ ይስማ አክለውም በቀጣይ ግን ከባለሙያዎች ጋር አብሮ በመነጋገር የጋራ አቅጣጫ በማስቀምጥ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም