የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ላይ ሚናቸው ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቆመ

85
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ላይ አዎንታዊ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ገለጹ። የአሜሪካየንግድተቋማትበኢትዮጵያምጣኔኃብትላይያላቸውንተጽዕኖበተመለከተበአዲስአበባየውይይትመድረክተካሂዷል። የአሜሪካ አፍሪካ የቢዝነስ ማዕከል ፕሬዚደንት ስኮት ኢስነር በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ አዎንታዊ ሚና ተጫውተዋል። በቀዳሚነትም የክህሎት ሽግግር በማምጣት፣ የሥራ ባህል ልማት እንዲጎለብት፣ በትምህርትና በጤና ልማት ላይ ደርሻቸው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት። በተለይም የሥራ እድል ፈጠራና የድህነት ቅነሳ መርኃ ግብር ላይ በማተኮር ማኅበረሰቡ ጠንካራ እንዲሆንም ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። በአካባቢ ጥበቃ ሥራ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን እንዲወጡ በማድረግ ድጋፍ ተደርጓልም ብለዋል። ይህም በድምሩ በኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የምጣኔ ኃብት እድገት እንዲረጋገጥ በማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት። ኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ቁጥር ለገበያ ተመራጭ እንደሚያደርጋት ገልጸው አገሪቷንም አካባቢውንም ለማሳደግ ትልቅ አቅም መኖሩን ገልጸዋል። የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በበኩላቸው የአሜሪካ የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል። ተቋማቱ በአገሪቷ ምጣኔ ኃብት አድገት ላይ ከሚያደርጉት አዎንታዊ ተጽዕኖ በዘለለ ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የአሜሪካ ተቋማት በኢትዮጵያ የሚካሄዱት የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በቀጥታ ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ነው ያስረዱት። በተለይም ከዩኒቨርስቲ ወጥተው የሥራ ልምድ ለሌላቸው ተማሪዎች በአሜሪካዊያን ስልጠና እና እገዛ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። በየዓመቱ የአገሪቷ ኢኮኖሚ በዓመት በአማካይ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ያስታወሱት ዶክተር ኤፍሬም፤ ዘንድሮ ግን ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የአሜሪካ ኢንቨስትተሮችና የአገር ውስጥ ባለኃብቶች ድጋፋቸውን እንዲያድርጉ ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም