የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በልዩ ስብሰባ እየመከረ ነው

68
ሀዋሳ ሐምሌ 4/2011 ( ኢዜአ) የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን /ማዕከላዊ ኮሚቴ በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በልዩ ስብሰባው እየመከረ እንደሚገኝ አስታወቀ። ድርጅቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ እንደገለጸው ማዕከላዊ ኮሚቴው ከሰኔ 28/20011ዓ.ም ጀምሮ ነው ልዩ ስብሰባውን እያካሄደ ያለው። በስብሰባውም ሀገራዊ እና ክልላዊ  ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በዝርዝርና በጥልቀት እየገመገመ ይገኛል፡፡ በክልሉ ህዝቦች የተነሱ የአደረጃጀት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አስመልክቶ ማዕከላዊ ኮሚቴው በሰከነና በኃላፊነት መንፈስ እየተወያየ መሆኑን ድርጅቱ  በመግለጫው አመልክቷል። እንደመግለጫው ውይይቱ  ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና  በሳል በሆነ መንገድ የህዝቡን የጋራና ዘላቂ ጥቅሞችን ለማረጋግጥ  የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ነው። ደኢህዴን በክልሉ ህዝቦች የተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በዝርዝር እና ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ሲያስጠና በቆየው ውጤት ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ኃላፊነት በተሞላበት አኳኋን እየመከረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በክልሉ ህዝቦች የተነሱ ጥያቄዎች በመሪ ድርጅቱ ደኢህዴን፣ በህዝቡ ፍቃድና ይሁንታ ብቻ ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጠው መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ልዩ ስብሰባውን ሲያጠቃልል ለአባላቱና ለክልሉ ህዝቦች እንዲሁም ለደጋፊ ኃይሎች ዝርዝር መረጃ የሚሰጥ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡ የክልሉ ህዝብም በሚቀርቡ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ በየደረጃው በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች እንዲሳተፍ እንደሚደረግም ገልጿል። ከዚህ ውጪ ህዝቡ በተለያዩ ኃይሎች በሚሰራጨው ውዥንብሮች እና የተሳሳቱ መረጃዎች ሳይደነጋገር በትግስት እንዲጠብቅ ደኢህዴን መልዕክቱን አስተላልፏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም