የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 45 ሺህ ቶን ምርት በ2 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር አገበያየ

63
ሀምሌ 4/2011(ኢ ዜ አ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር ውስጥ ግብይት በተካሄደባቸው 19 ቀናት 45 ሺህ ቶን ምርት በ2 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ገለጸ። በቅርቡ ምርት ገበያውን የተቀላቀለው ሽምብራ 40 ቶን ሊገበያይ ችሏል። በወሩ 26 ሺህ 137 ቶን ቡና፣ 11 ሺህ 409 ቶን አኩሪ አተር፣ 5 ሺህ 760 ቶን ሰሊጥ፣ 1 ሺህ 728 ቶን ነጭ ቦለቄ እና 40 ቶን ሽምብራ በ2 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። በተያዘው አመት በታህሳስ ወር ወደ ግብይት ስርዓቱ የገባው ሽምብራ 400 ኩንታል ለገበያ ቀርቦ በ772 ሺህ ብር ተሽጧል፤ በተመሳሳይ ወቅት ወደግብይቱ የገባው አኩሪ አተር  በመጠንና በዋጋ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ 11ሺህ 409 ቶን በ177ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል። የአኩሪ አተር ግብይት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሐምሌ 03 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ 92 ሺህ 103 ቶን ምትር በ1 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር መገበያየቱን መግለጫው አመልክቷል። በሰኔ ወር ቡና የግብይቱን 58 እና 76 በመቶ በግብይት መጠንና ዋጋ ቀዳሚ ሲሆን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በግብይት መጠንና ዋጋ ተመሳሳይ 62 በመቶ ይዞ ቀዳሚ ሆኗል። በወሩ 15 ሺህ ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ያልታጠበ ቡና በ1 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር ተሽጧል። 923 ቶን የታጠበ ቡና በ60 ነጥብ 7 ሚሌን ብር በውጭ ገቢያ መሸጡን በመግለፅ ሲዳማ ቡና የግብይቱን 40.6 በመቶ የመሆነውን ይዟል የተባለው። በዚህ ወር 5ሺህ 760 ቶን ሰሊጥ በ351 ነጥብ 66 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 18 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሲኖረው 11 በመቶ የመጠን ቅናሽ አሳይቷል። 1 ሺህ 728 ነጭ ቦለቄ በ35 ነጥብ 54 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር መጠኑ 24 በመቶ ቢቀንስም የግብይት ዋጋው 1 ነጥብ 38 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም