በሐረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ ነው

92
ሐረር ሀምሌ 4/2011(ኢ ዜ አ)በሐረሪ ክልል ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እየተነቃቃ በመምጣቱ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ገለፀ ፡፡ በቢሮው የቱሪዝም ዳይሬክተር ወይዘሮ ያስሚን ዘካሪያ እንደገለፁት ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱና በክልሉ ተከስተው በነበሩ የፀጥታ መደፍረስና ሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ተቀዛቅዞ ቆይቷል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉና በከተማዋ የሚገኙ ኃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎችን በ23 ሺህ 553 የውጭ ቱሪስቶች ጎብኝተዋል። ይህም ከቀዳሚ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ42 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል ። "ለጎብኚዎቹ ቁጥር መጨመር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱና በክልሉ እየታየ የሚገኘው አንጻራዊ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል በማሳየቱ ነው" ብለዋል ። በበጀት ዓመቱ  ከ112 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በከተማው የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በመጎብኘት ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል። የውጭ ቱሪስቶችን በማስጎብኘት ስራ የሚተዳደሩት አቶ አብዲ አህመድ በሰጡት አስተያየት "ባለፉት ሶስት ዓመታት ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲቀንስና እለታዊ ገቢያችን ጭምር እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኖ ነበር "ብለዋል ። በአሁኑ ወቅት የሚታየውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው የሆቴሎች መስፋፋትና የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል ጎብኚዎች በአካባቢው ውለው እንዲያድሩ መነሳሳት እየፈጠረ መምጣቱን ያስረዳው ደግሞ በአስጎብኚነት ስራ የተሰማራው ወጣት ቢኒያም ወልደሰማያት ነው። የጀጎል ቅርስ ከመጠበቅና በተለይ ደግሞ ክልሉን ከማስተዋወቅ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ስራዎች ዝቅተኛ በመሆናቸው የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም ጠቁሟል። የክልሉ ባህል ፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አዩብ አብዱላሂ በበኩላቸው "በተለይ በጀጎል ግንብ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቤቶችና አድባራትን የማደስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል "ብለዋል ። በክልሉ ታሪካዊና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። በሐረሪ ክልል በቱሪስቶች ከሚጎበኙት ቅርሶች መካከል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊ የጀጎል ግንብ ፣ በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች ፣ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች ፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቦ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞች ፣አድባራትና የጅብ ምገባ ትርኢት ይጠቀሳሉ ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም