በምዕራብ አፍሪካ የፀረ ሽብርተኝነት ትግሉ አመርቂ እንዳልሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ዋና ፀሃፊ ተናገሩ

62
ኢዜአ ሃምሌ 4/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በምዕራብ አፍሪካ ሳሃል ቀጠና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አመርቂ እንዳልሆነ መናገራችውን ቢቢሲ ዘግቧል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ወቅት ዋና ፀሃፊው ለጋሾች ሽብርተኝነትን እና ፅንፍ የወጣ አክራሪነትን ለመከላከል ለወታደራዊ ሃይሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘገባው አስታውሷል። ከቅርብ ጊዜ ውዲህ በሳሃል ቀጠና የጎሳ ግጭት እና ጂሃዲስቶች እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የሁለቱም ጥምረት እየተስፋፋ በመምጣቱ ከፍተኛ ጉዳት በቀጠናው እያደረስ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። ጂ 5 ሳህል የተሰኘው የአካባቢው የፀረ-ሽብር ሃይል በቂ የገንዝብ አቅም ስለሌለው ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አሸባሪ ቡድኖች እና አይ ኤስ ከተሰኘው ፅንፈኛ ቡድን ጋር የሚያደርገው ፀረ-ሽብር ትግል ስኬታማ ሊሆን እንዳልቻለ ዘገባው ጠቁሟል። በአካባቢው የተሰማራው የፀረ ሽብር ሃይል በአመለካከትና በሚወስደው ተልዕኮ ረገድ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እገዛን እንደሚሻ ጉቴሬዝ አሳስበዋል። የአምስቱ የሳሃል ቀጠና ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በዘገባው ሰፍሯል። በዚህ ሳምንት የአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ የ150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሳሃል ቀጠና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ ለሚገኘው የሳሃል ኃይል ድጋፍ አድርጓል፤ ይሁን እንጂ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ለጋሽ ተቋማት በቃላችው እንዳልተገኙ መረጃው አትቷል። ምንም እንኳን የቡድን አምስት የሳሃል ቀጠና ከተመሰረተ ሁለት አመታትን ያሰቆጠረ ቢሆንም ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ሊያደርግ አልቻለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም