የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 18 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በጀት አፀደቀ

179

ጂግጂጋ  ሐምሌ 4/2011 (ኢዜአ) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2012 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል 18 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በጀት አፀደቀ።

በጀቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ646 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙበሽር ዱበድ ትላንት ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት  ማብራሪያ በጀቱ የሚሸፈነው ከፌደራል መንግስት ድጎማ ፣ ከውጭ ድጋፍ ፣  ከክልሉ የውስጥ ገቢ እና  ከድህነት ቅነሳ ፈንድ ነው ።

ከበጀቱ ውስጥ 7 ቢሊዮን ብሩ የአርብቶ አደሩን ፍላጎት መሰረት ላደረጉ የልማት ስራዎች ማስፈሚያ የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።

አዳዲስና ነባር የውሀ ተቋማት እንዲሁም የመንገድ ግንባታ፣ የስራ እድል ፈጠራና  የግብርና ልማት ስራዎች በበጀት ዓመቱ በትኩረት የሚከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በዘጠኝ ዞኖች የአርብቶ አደሩ ልጆች አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡም አስረድተዋል።

በሺኒሌ፣ ገርቡና ዋርዴር ከተሞች አዳዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንደሚገነቡና 150 ጤና ጣቢያዎች በህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እንደሚደራጁ ጠቅሰዋል ።

የምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን በጀት በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል ።

በተጨማሪም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርትም በአባላቱ   ውይይት ተደርጎበት ፀድቋል ።

የምክር ቤቱ ጉባኤ በተጨማሪም  በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ሦስት የምክር ቤቱ አባላት ያለ መከሰስ  መብት ለማንሳት የቀረበው ውሳኔ ለተጨማሪ እይታ ለምክር ቤቱ የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማምራት  መረሀ ግብሩን ትናንት ማምሻውን አጠናቋል።