የሱዳን ተፎካካሪዎች ልዩነቶቻቻውን በሰላም እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ፊንላንድ አደነቀች

84
ሐምሌ 3 / 2011( ኢዜ አ) ኢትዮጵያ የሱዳን ተፎካካሪ ኃይሎች ልዩነቶቻቻውን በሰላም እንዲፈቱ የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፊንላንዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በትምህርትና የስራ ፈጠራ ዘርፎች በምታከናውናቸው ተግባራት አገራቸው እገዛ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል። በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ባሉ የለውጥ ስራዎች ፊንላንድ ደስተኛ መሆኗንም ተናግረዋል። ሂደቱ በዚህ ከቀጠለ ለኢትዮጵያዊያን የተሻለ የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የስራ ዕድል እንደሚፈጠርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አገራቸው ይህን ለመደገፍ የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ በመጠቆም። ኢትዮጵያ የሱዳን ተፎካካሪ ኃይሎች ልዩነቶቻቻውን በሰላም እንዲፈቱ እያደረገች ባለው ተግባር አገራቸው ደስተኛ መሆኗንም ነው የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ረገድ ያበረከቱትን ሚና አድንቀዋል። የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ በቅርቡ ኢትዮጵያን የመጎብኘት እቅድ መያዛቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ዮንግ ዋን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ውይይታቸው በዋናነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረውን የኢትዮ-ኮሪያ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አገራቸው በጦርነት ወስጥ ሆና ኢትዮጵያ ዜጎቿን ልካ እገዛ እንዳደረገች አስታውሰው፤ ሁነቱ የሁለቱ አገራት ልዩ ወዳጅነት ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል። ኮርያና ኢትዮጵያ በቀጣናቸው ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም አውስተዋል። ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ ሁለቱ አገራት ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሩ አጋጣሚ  እንደሚፈጥርም አብራርተዋል። ውይይቱን የተከታታሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ኢትዮጵያዊያን ወደ ኮርያ አቅንተው የትምህርትና ስልጠና ዕድል በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የጉምሩክና ገቢዎች አሰራርን ለማዘመን በምታደርገው ጥረት የኮርያ ድጋፍ ምን መምሰል አለበት የሚለውም የውይይቱ አካል እንደነበር ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኮርያን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸውንም አክለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም