በአማራ ክልል የተሻሻሉ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ ተጀመረ

207
ባህርዳር/አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ሐምሌ 3/2011 በአማራ ክልል በ18 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ13 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እቅንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ ትናንት ከ5 ሺህ በላይ ችግኞች እንደተተከሉ ተመልክቷል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የቡና ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ እየተተከለ ከሚገኘው ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የቡና ተከል ችግኝ ነው። ቀሪ ችግኞች የአቦካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን፣ ፓፓያና  አፕል ጨምሮ የተለያዩ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ናቸው። የቡና ችግኞች በ20 ወረዳዎችና ፍራፍሬዎቹ  ደግሞ በ38 ወረዳዎች በተለዩ ኩታገጠም  የእርሻ ማሳዎች እንዲሁም  በሌሎች መደበኛ የተከላ ቦታዎች እየተከናወነ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል። በቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ስራ ላይ ከ146 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከለው 12 ሚሊዮን 400ሺህ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኝ ውስጥ 83 በመቶ ያህሉ መጽደቁን ጠቁመዋል። በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የሮቢት ባታ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ዋለ ደጉ ቀደም ሲል ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት  ቡና ስድስት ኩንታልና ማንጎ ደግሞ ሁለት የጭነት አይሱዙ የሚሆን አምርተው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተያዘው የክረምት ወቅትም ተጨማሪ 300 የማንጎ ችግኞችን በግማሽ ሄክታር መሬት መትከላቸውን አመለክተው  ተጨማሪ የተከተቡ 200 የአቦካዶ ችግኞችን ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ወስደው ለመትከል በዝግጅት ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል። በወረዳው ይጎዲ ቀበሌ  "መንገሻ፣ ዘላለምና ጓደኞቻቸው የሙዝ ልማት ሽርክና ማህበር " በሚል ከተደራጁት ውስጥ አባል የሆነው ወጣት ዘላለም እንዳለው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የሙዝ ተክል በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል። በክልሉ  በቡና ተክል ከተሸፈነው 17 ሺህ 816 ሄክታር መሬት 14 ሺህ ሄክታሩ ምርት መስጠት መጀመሩንም ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተመሳሳይ በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ከ5 ሺህ በላይ ችግኞች መትከሉን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የችግኝ ተከላው ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸዋል። "በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ችግኝ መትከል ያስፈልገው ፓርኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጎዳ መምጣቱን ተከትሎ ነው " ብለዋል። የጋሞ ዞን አስተዳደርና የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የስራ ኃላፊዎች የአከባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ዘነበ በበኩላቸው ችግኞቹ  መትከላቸው ለፓርኩ ስነ ምህዳር መጠበቅ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ትናንት  በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ጨምሮ ከጋሞ ዞን ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማና ከዙሪያው  ወረዳ እንዲሁም ከፓርኩ የተወጣጡ ከ400 በላይ ሰዎች ተሳታፊ ነበሩ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም