የፈጠራ ባለቤቶች ዕውቀታቸውን በንብረትነት በማስያዝ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው

40
ሀምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) የፈጠራ ባለቤቶች ዕውቀታቸውን በንብረትነት በማስያዝ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ ኃይለማሪያም እንደገለጹት የፈጠራ ባለሙያዎች እውቀታቸውን በንብረትነት በማስመዝገብ ከባንክ ብድር በማግኘት እንዲሰሩ የሚያስችል አሰራር ለመጀመር ጥረት እየተደረገ ነው። በስራ ላይ ያለው የብድር ስርዓት የማይዳሰሱ የፈጣራ ዕውቀቶችን በንብረትነት ይዞ የብድር አገልግሎት እንደማይፈቅድ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል። የአገሪቱን የፈጠራ ሰዎችን በኢኮኖሚው ለማሳተፍና የፈጠራ ዕውቀታቸውን በንብረትነት በመያዝ ከባንኮች ብድር እንዲያገኙ ፅህፈት ቤቱ ጥረት ያደርጋል ብለዋል። ላለፉት 20 ዓመታት ያገለገለውን የአዕምሯዊ ንብረት ህግ በማሻሻል የፈጠራ ዕውቀት ዋጋ ትመና እና ሌሎችንም ያካተተ አዲስ አሰራር ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ፅህፈት ቤቱ 38 አገሮችን በአባልነት ከያዘውና መቀመጫውን ሙኒክ ካደረገው የዓለም አቀፉ ፓተንት ጽህፈት ቤት ጋር በትብብር በመስራትም ላይ ይገኛል። በዚህም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታትና በፈጠራ ስራቸው ብድር እንዲመቻችላቸው የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል። በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ ፈጠራን በማሳድግና አጠቃላይ የጽህፈት ቤቱን ስራዎች በማሳለጥ እንዲሁም ዲጂታል በማድረግ ሂደት ድጋፍ ያደርጋል። እንደ አቶ ኤርምያስ ገለፃ ዓለም አቀፉ የፓተንት ፅህፈት ቤትም  አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድርግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል። ባለፈው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በፈጠራ፣ ጥበብ፣ በምርምር እንዲሁም የፓተንት ህግን ጨምሮ ከ27 በሚልቁ ጉዳዮች በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ስልጠና መስጠቱንም ጠቅሰዋል። በ2011 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ከተመዘገቡት 3 ሺህ 245 ተገልጋዮች 1 ሺህ 980 የሚሆኑት የውጭ ዜጎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። በ2011 ዓ.ም በአለም ከቀረቡት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የፈጠራ መብት ጥያቄዎች 1 ነጥብ 9 ሚሊየኑ በቻይናውያን የቀረበ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም