የተፈናቀሉ 50 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመልሶ ማቋቋምና ማገገም ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

106
ሀምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ 50 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመልሶ ማቋቋምና ማገገም ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም አስተባባሪነት የሚከናወነው ይህ ፐሮጀክት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ይፋ የተደረገ ሲሆን 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዋና ኃላፊ ሚስተር ቱርሀን ሳሌህ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በዋናነት በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ከደረሰባቸው ጉዳት አገግመው ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ያለመ ነው ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸው 50 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ፕሮጀክት 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚከናወን አመልክተዋል ፡፡ “በመጀመሪያው ዓመት አምስት ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ከአምስት ሺህ ቤተሰቦች በላይ ድጋፍ ይደረግላቸዋል” ብለዋል፡፡ ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚውል ከጃፓን መንግስት 1 ሚሊዮን ዶላር ከዴንማርክ መንግስት ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል ፡፡ ቀሪው ገንዘብ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሚሸፈን መሆኑን አመልክተዋል። ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን የፌዴራል እንዲሁም የኦሮሚያና ደቡብ ክልል መንግስታት ድጋፍ የማይተካ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሰብዐዊ ድጋፍና ዓደጋ መከላከል ሥራ ላይ ለወደፊቱም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ሚስተር ቱርሀን አስረድተዋል ፡፡ “ፕሮጀክቱ በዋናነት በቤቶች ግንባታ፣ በግብርና ግብዐት አቅርቦትና በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተለይ ሴቶችና ወጣቶችን በነዚህ ሥራዎች ላይ በማሳተፍ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል ብለዋል ፡፡ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መኮንን ለንጊሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ሰብዐዊ ድጋፍ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ዓለም አቀፍ ተቋማት ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም እንዲሁም የጃፓንና ዴንማርክ መንግስታት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ከሰብዐዊ ድጋፍ ተላቀው ወደ ቀድሞው መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ  በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ በተለይ በመኖሪያ ቤት ግንባታና በግብርና ግብዐት አቅርቦት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል ፡፡ ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ እንደሆነ ገልፀዋል ፡፡ ፕሮጀክቱ በግጭቱ በተለይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ማዕከል አድርጎ የሚከናወን ሲሆን ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ እና ሀምበላ ዋመና ወረዳዎች እንዲሁም ከጌዴኦ ዞን ደግሞ ገደብና ይርጋጨፌ ወረዳዎች ተመርጠዋል ፡፡ በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብር ላይ የጃፓንና የዴንማርክ መንግስታት ተወካዮች፣  የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም የዞን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም