ከኮሌራ ወረርሽኝ ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል

54
ሃምሌ 2/2011 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ እየቀነሰ ቢሆንም ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ። ኢንስቲትዩቲ የበሽታውን ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የበሽታውን ወረርሽ በተመለከተ በተደረገው ክትትል በኮሌራ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት አንጻር ሲታይ ቀንሷል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ እንደገለጹት፤ በአማራና በሶማሌ ክልሎች ተከስቶ የነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ ከቆመ ከአንድ ወር በላይ ስለሆነው ክልሎቹ በአለም አቀፍ የጤና ድርጅት መመሪያ መሰረት ከወረርሽኑ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል። በሌሎች አካባቢዎችም በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጥቱን ጠቅሰው፤ ''ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል'' ሲሉ አሳስበዋል። በዚህ ሳምንት በአገር አቀፍ ደረጃ 44 ሰዎች በበሽታው ተይዘው የነበረ ሲሆን ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፃር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል። ለዚህም የኮሌራ ክትባት መጀመሩ፣ የተበላሹ የቧንቧ ውሃ መስመር ላይ ጥገና እንዲከናወን መደረጉና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸው ለወረርሽኑ መቀነስ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካበቢዎች ስርጭቱን ለመግታት የግልና የአካበቢ ንጽህና አጠባበቅ ስራ መሰራቱ፣ ከነዋሪዎች አኗኗር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የንጽህና አጠባበቅ ችግሮች እንዲቀረፉ የሚያደርግ ስራ መከናወኑና የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቦታ እንዲመቻች መደረጉ ሌላው ምክንያት መሆኑን አክለዋል። የተፈናቀሉ ሰዎችና ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ዜጎች የአካባቢና የግል ንጽህናን እንዲጠብቁ  የሚያስችል የሳሙና፣ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ፣ ጀሪካኖች፣ የውሃ  ማከሚያ  ኬሚካሎችና ቁሳቁሶችን እየቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል። በቀጣይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በዓል ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብበት በመሆኑ በዓሉ በሚከናወንት አካባቢዎች ወረርሽኙ እንዳይከሰት ከሚለከተቻው አካላት ጋር  የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል። በዚህም ከ400 በላይ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ተሳታፊ በማድረግ የመከላከል ስራው እንደሚሰራ ዶክተር በየነ  ተናግረዋል። የኮሌራ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙን ለመከላከል ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም