ውሳኔው ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚጠቅም ነው --- ምሁራን

61
መቀሌ ሰኔ 3/2010 ኢትዮ - ኤርትራን አስመልክቶ በቅርቡ የኢሀአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ  ያስተላለፈው ውሳኔ  ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ሰላም የሚጠቅም  መሆኑን የመቀሌና  ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎች  ምሁራን ገለጹ፡፡ ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት ውሳኔው ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚጠቅም ከመሆኑ ባለፈ በአፍሪካ  ህዝቦች ውህደት ለመፍጠር  የሚደረገውን ጥረት የሚያበረታታ ነው፡፡ በድንበር ጉዳይ ላይ ለብዙ ዓመታት ጥናት ማድረጋቸውን የተናገሩት  የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁሩ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ህዝቡ በተለያዩ መደረኮች ከድንበር  ጋር ተያይዞ ሲያነሳቸው የቆዩ ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው፡፡ "በደም የተሳሰሩት የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ልማታቸውን የሚያረጋግጡበት የውሳኔ እርምጃ በመሆኑ ህዝቦቹ ለተግባራዊነቱ ሊረባረቡ ይገባል "ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር  የማነ ዘርአይ በበኩላቸው ውሳኔው ሁለቱም ህዝቦች የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ለመዋጋት የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል። የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ድንበር ላይ ላለፉት ዓመታት ሲኖሩ መቆየታቸውን አመልክተው ስራ አስፈጻሚው ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ያሳለፈው  ውሳኔ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ውሳኔው ላለፉት 20 ዓመታት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱንም ሀገራት ግንኙነት ችግር ሊፈታ እንደሚችል ገልጸው  በተለይም ከኤርትራ እየተነሱ የሀገሪቱን  ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ስርዓት እንደሚያስይዝ ተናግረዋል። በዓዲግራት ዩኒቨርስቲ የስነ ምግባርና ስነ ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር ተክሌ ተስፋማርያም በበኩላቸው "ውሳኔው ህዝብን ከህዝብ ለማቀራረብ የሚጠቅም በመሆኑ ይደገፋል "ብለዋል፡፡ አፈፃፀሙ ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ምሁራኑ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲረግብና ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲመለስ በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ለአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊነት እንደሚሰራ ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም