ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን በትኩረት ሊሰራ ይገባል - የዘርፉ ተመራማሪዎች

79
ጎባ ሰኔ 3/12010 በግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የሚታዩትን ተግዳሮቶች በጥናትና ምርምር በመደገፍ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስተር ጋር በመተባበር “ ዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ጥቅም ለግብርና ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት አንደኛው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ  በባሌ ሮቤ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ከኮንፈረንሱ ተሳታፊ ተመራማሪዎች መካከል የኦሮሚያ ግብርና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ እስሞ እንደተናገሩት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ለሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የግብርናው ሴክተር የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው ፡፡ ''የግብርናው ስራ በውጤታማነት እንዲዘልቅ ለማስቻል የግብርና ምርምር ስራዎች በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በጥናት በመደገፍ በአዲስና ችግር ፈቺ አቅጣጫ መመራት ያስፈልጋል'' ብለዋል፡፡ ተመራማሪው እንዳሉት ከእጅ ወደ ኣፍ የሆነውን ግብርናችንን በተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማገዝ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲሆን የዘርፉ ተመራማሪዎች ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና ተመራማሪ ወይዘሮ ሰብለ ሙሉጌታ አማራጭ ኃይል ላይ ባቀረቡት የምርምር ጽሁፍ ላይ እንደገለጹት ማህበረሰቡ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ እያደረሰ የሚገኘው ጉዳት በግብርና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው፡፡ ''ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ሶላርና ባዮ ጋዝን የመሳሰሉ የኃይል አማራጮችን ተደራሽ በማድረግ ግብርናውን ውጤታማ ለማድረግ ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡ በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስተር የደን እስትራቴጂ ድጋፍ  ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ሚናሴ ጋሻው እንደተናገሩት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትር መር የሚደረገውን ሽግግር ለማቀላጠፍ የአየር ንብረት ለውጥን ያገነዘበ ግብርና ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል፡፡ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማህበረሰብ አቀፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር መሰረት ያደረጉ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የአርሶና አርብቶ አደሩን ከተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ጋር በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትቱን ለማሳደግ የምርምር ጣቢያዎችን በሮቤ፤ጊኒርና መዳ ወላቡ ወረዳዎቸ ከፍቶ እየሰራ መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓ ም ጀምሮ ከ390 በላይ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረት ያደረገውና ትናንት የተጀመረው አንደኛው አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የግብርና ምርምር ተቋማት የተጋበዙ ተመራማሪዎች ከ23 በላይ ምርምሮች አቅርበው እየተወያዩበት ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም