መንግስት በአዲሱ በጀት ዓመት ኃብት ሊፈጥሩ በሚችሉ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ

91
አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2011/ኢዜአ/መንግስት አዲስ በተጀመረው በጀት ዓመት ኃብት ሊፈጥሩ በሚችሉ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2012 ዓም በጀት ዙሪያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ  ላይ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ የሚታዩ የተፈጥሮ ኃብቶች እያሏት ነገር ግን በዛው ልክ መጠቀም ያለመቻሏን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሁኔታ በተወሰነ መልኩ መቀየር የሚያስችል ሥራ  በአዲሱ በጀት ዓመት ይከናወናል ብለዋል። በዚህም ከግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቀጥሎ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽኖኦት ሰጥዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በቀጣይ በጀት ዓመት ሊሰሩ ይችላሉ ከተባሉ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች  መካከል የተወሰኑትን ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል። ለአብነትም በአርባ ምንጭ ትልቅ የሆቴል ሪዞርትን ጨምሮ በአዲስ አበባ አካባቢ እየተገነቡ ያሉ እና ሊገነቡ የታሰቡ ፕሮጀክቶችን አንስተዋል። ሲሸልስ ከአንድ ሆቴል ሪዞርቷ ብቻ የምታገኘው ገቢ በአገሪቱ ከአብዛኛው ሴክተር ከሚገኘው ገቢ በእጅጉ የበለጠ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ይህን ሥራ ወደአገር ቤት በማምጣት ከዘርፉ መጠቀም እንደሚቻል አስረድተዋል። በመሆኑም በአርባ ምንጭ ያለውን የተፈጥሮ ስጦታ ተጠቅሞ ከሲሸልሱ ጋር ተቀራራቢ የሆነ የቱሪስት መዳረሻ ሆቴልና ሪዞርት ለመገንባት ከለጋሽ አካላት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሚገኝበትን እና ታላቁ ቤተ መንግስትን ጨምሮ የፕሬዚዳንቷ ጽህፈት ቤት የሆነው የብሄራዊ ቤተ መንግስት በቀጣይ ወራት ውስጥ ለህዝብ ክፍት በማድረግ ሀብት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ፕሬዝዳንት ቢሮዎችን በአንድ ግቢ ውስጥ በማሰባሰብ ያለውን ኃብት በጥንቃቄ እና በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በንጉሱ ዘመን ተገዝተው የነበሩ ካዲላክ የተሰኙ የቤተ መንግስት እንግዳ መቀበያ ተሽከርካሪዎች በቤተመንግስት የእቃ ግምጃ ያለ ጥቅም ተቀምጠው ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ሁኔታ ለመቀየር መኪኖቹ የሚጎበኙበትን እና ከዚህም ሀብት ሊመነጭ የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ከፓርላማው ፊት ለፊት ከሚሰራው ቤተ መጽሀፍት ጀምሮ እስከ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሚሰራው ፓርክ  ጨምሮ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ከማድረግም በላይ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል። እነዚህ ውጥኖች እንዲሳኩ መንግስት በቁርጠኝነት በመስራት በርካታ ኃብት ወደአገር ውስጥ እንዲፈስ እና ዜጎች የስራ እድል እንዲያገኙ በማድረግ ህይወታቸው በዘላቂነት እንዲቀየር እንደሚሰራ አክለዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም