የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ በጀትና አዋጆችን በማጽደቅ ማምሻውን ተጠናቀቀ

78
መቀሌ ሰኔ  30/2011  (ኢዜአ ) የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ ለ2012 የስራ ዘመን 16 ቢሊዮን 700ሚሊዮን ብር በጀትና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ ማምሻውን ተጠናቀቀ። በምክር ቤቱ የበጀትና ኦዲት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሰ ለገሰ እንዳስታወቁት  በጀቱ የሚሸፈነው  ከፌዴራል መንግስት ድጎማ ፣ከተለያዩ የውስጥ ገቢዎችና በብድር  ነው። በጀቱም በዘመኑ ለመደበኛ እና ለካፒታል ፕሮጀክት እንዲሁም ለመጠባበቂያ  መደልደሉን ገልጸዋል። ለካፒታል ፕሮጀክት ከተያዘው በጀት 61 በመቶ የሚሆነው ለድህነት ተኮር እንደሚውል ያመለከቱት አቶ ንጉሰ በዋነኛነትም ለውሃ ሃብትና  ለግብርና ስራዎች ቅድሚያ መሰጠቱን አስረድተዋል። ጉባኤው በተጨማሪም የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም ትእምት/ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን የሚደነግገው አዋጅ ጨምሮ የተለያዩ አዋጆች መርምሮ አፅድቋል። ከዚህ ሌላ የክልሉ ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በክልሉ የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥና ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን በምክር ቤቱ የህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ሞገስ ታፈረ  ገልጸዋል። የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ  ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ ግልፅነት የሌላቸውና ከክልሉ  ህገመንግስትም ሆነ ከፌዴራሉ አዋጅ ጋር የሚጣረሱ አንቀፆች እንዳሉባት በማመልከት  ለቀጣይ ተስተካክሎ እንዲቀርብ በማለት ውድቅ አድረገውቷል። ለአራት ቀናት በመቀሌ  ከተማ ሲካሄድ የቆየው ክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ የስራ ዘመን 16 መደበኛ ጉባኤ መረሀ ግብሩን  ማምሻውን አጠናቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም