ኮሌጁ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም ድጋፉን ማጠናከር አለበት--- ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ

52
ኢዜአ ሃዋሳ  ሰኔ 30/2011  የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እንደሃገር የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት የኢፌድሪ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ አሳሰቡ፡፡
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የተገኙት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ኮሌጁ በሃገሪቱ ቀዳሚና ብዙ ልምድ ያለው ያለው ነው። የተካበተ ልምዱን በመጠቀም  የሚሰጠው ትምህርትና የሚያከናውነው ምርምሮች ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በሃገሪቱ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ኮሌጁ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል። ሃገሪቱ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ አልምቶ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ልማት ለማዋል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ መሆኑን  ፕሮፌሰር ፍቃዱ ተናግረዋል። የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አቶ አያኖ በራሶ በበኩላቸው ተቋሙ የህዝብ ጥግግት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የደን መመናመንና የአየር መዛባትን ለማስቀረት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ " በቀጣይም በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለመቀጠል ከፍተኛ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው "ብለዋል፡፡ ኮሌጁ በመጀመሪያ ፣በሁለተኛና በሶስተኛ ድግሪ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት 819 ተማሪዎችን ማስመረቁን የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ ዲን ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ናቸው፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 45 በመቶው ሴቶች ናቸው። "በመደበኛ በጀት ከሚከናወኑ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎቶች በተጨማሪ በሃገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙ አጋር ተቋማት ጋር በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው "ብለዋል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ዘረፍ በሶስተኛ ዲግሪ የተመረቀው  ሃጂ ከድር የአለምና የሃገር ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ችግር ፈቺ ምርምሮች በማከናወን የበኩሉን  እንደሚወጣ ተናግሯል። ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም እስከ ታች ያለውን ማህበረሰብ በአረንጓዴ ልማት ግንዛቤውን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ ታዳሽ ሃይል ላይ ትኩረት አድርጎ ሁለተኛ ዲግሪውን የሰራው አማኑኤል አሰፋ በበኩሉ የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል ባህላዊውን የኃይል አጠቃቀም መቀየር እንደሚያፈልግ ገልጿል፡፡ ለዚህም አማራጭ ታዳሽ ሃይል በመጠቀም የሚጨፈጨፉ ደኖችን መቀነስና አዳዲስ ችግኞችን በመትከል እንደሃገር የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግሯል፡፡ ኮሌጁ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂዎችንም ሸልሟል፡፡
   
     
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም