ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው 'አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል' ተመረቀ

168
ሰኔ 30/2011 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው 'አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል' ተመረቀ። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች በተገኙበት የተመረቀው ሆስፒታሉ 80 አልጋዎች ያሉት ሲሆን ለ200 ያህል ሰዎች የሥራ እድል ፈጥሯል። ሆስፒታሉ አጠቃላይ የህክምና አገልግሎት የሚያቀርብ ሲሆን በተለይም የጉበት፣ ጨጓራና አንጀት ህክምናዎችን በልዩ መልኩ ይሰጣል ተብሏል። ሆስፒታሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመደራጀቱ በተጨማሪ በህክምናው ዘርፍ የሚወጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተናገድ በሚችል መልኩ የተገነባ ነው ሲሉ የሆስፒታሉ ባለቤት ዶክተር መሀመድ ሽኩር በምረቃው ላይ ገልፀዋል። በመሆኑም ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ሲደራጅ ዜጎች ለህክምና ወደውጭ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ እና ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪ የጎረቤት ሀገራት ታካሚዎችም ወደኢትዮጵያ በመምጣት ደረጃውን የጠበቀ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል። ግንባታው አምስት ዓመት የፈጀው አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል  80 አልጋዎች ያሉት ሲሆን የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን፣ የውስጥ ደዌ፣ የማህፀንና ፅንስ፣  የህፃናት፣ የዓይንና የጥርስ እንደዚሁም የልብ፣ የመተንፈሻ አካላትና መሰል ህክምናዎችን ይሰጣል። የህክምና ላቦራቶሪዎቹ በብቁ ባለሙያዎችና አለም አቀፍ መስፈርተን ተከትለው የተደራጁ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር መሐመድ የሲቲ ስካንና ኤም አር አይ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሆነም ገልፀዋል። በምረቃው ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው" የግል ባለኃብቱ በሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል። መንግስት በሽታን በመከላከል ላይ በማተኮር የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎትን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ አመልክተዋል። በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን የማጠናከሩ ተግባር የሚከናወነው ደግሞ ከግል ባለኃብቱ ጋር በመተባበር እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም የግሉ ዘርፍ ከውጭ ባለኃብቶች ጋር ጭምር ተባብረው የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና የመንግስትና የግል ዘርፉ አጋርነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል። ዶክተር መሀመድ ከዚህ በፊት የመክፈል አቅም ለሌላቸው ነፃ ህክምና በመስጠት የሚታወቁ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የጤና ሚኒስትሩም ዶክተር መሀመድ ይህንን ተግባራቸውን አሁንም አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አደራ ብለዋል። በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ልዩ ስሙ ኮካ በሚባለው አካባቢ የተገነባው አሚን ሆስሚታል ነገ ኃምሌ 1 ቀን 20011 ዓም ሥራ ይጀምራል፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየው በቦሌ የሚገኘው ሆስፒታልም ለአንድ ወር ያህል አገልግሎት መስጠቱነ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም