በጌዴኦ ሞተር ብስክሌቶች የትራፊክ አደጋን እያባባሱ ነው

145
ሰኔ 30/2011 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የሚንቀሳቀሱ ሞተር ብስክሌቶች የትራፊክ አደጋውን ከማባባስ ባሻገር ለወንጀል መፈፀሚያ አገልግሎት እየዋሉ በመሆናቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ተጠየቀ ። የትራፈክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር በዲላ ከተማ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የእግር ጉዞና የምክክር መድረክ ትናንት ተካሔዷል ። ነዋሪዎቹ በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ እየጨመረ ለመጣው የትራፊክ አደጋ የባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶች አሉታዊ ተፅእኖ የጎላ ነው፡፡ ከዲላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል መምህር ጌታምህረት ገብሩ በሰጡት አስተያየት እድሜያቸው ለማሽከርከር ያልደረሱ ልጆች ጭምር  ሰሌዳ የሌላቸው  ህገ ወጥ ሞተር ሳይክሎችን ሲያሽከረክሩ መመልከት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች መበራከቱን ተከትሎ የትራፊክ አደጋ እንዲባባስና የወንጀል ድርጊቶች እንዲጨምሩ እያደረገ በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ጠይቀዋል ። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ በረከት በራሶ በበኩላቸው "በዞኑ የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሁላችንም ተባብረን ልንሰራ ይገባል "ብለዋል ። የትራፊክ ፍሰት ተቆጣጣሪዎች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ትርፍ መጫንንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈልን መብት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። ድርጊቱ ህብረተሰቡን ለተጨማሪ ወጪና ለእንግልት ከመዳረጉ ባለፈ ለትራፊክ አደጋ  መንስኤ ሆኗል። የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ዋቆ እንዳሉት  በጌዴኦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተመዘገቡት 43 የሞት አደጋዎች ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የሚይዘው በባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሞተር ብስክሌቶችም ሆነ የሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ህጋዊ መሰረት ባይኖረውም አደጋውን ለመቀነስ ሲባል ብቻ  ሞተረኞችን በማደራጀት የተለያዩ ትምህርቶችን ለመስጠት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል:: በዞኑ የመንግስትን ጨምሮ በርካታ ሞተር ብስክሌቶች  ሰሌዳ እንደሌላቸው ያመለከቱት ኃላፊው "ሰነድ ያላቸው ባለንብረቶች ህጋዊ መስመሩን እንዲከተሉና ህገ ወጥ የሆኑትን ደግሞ እንዲቆሙ ይደረጋል "ብለዋል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው በዞኑ በየቀኑ የሚሰማው የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ 10 ሺህ የሚደርሱ ሞተር ብስክሌቶች በኮንትሮባድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡና ህገወጥ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ሞተር ብስክሌረቶቹ ህገወጥ ቢሆኑም ለወጣቶች የፈጠሩት የስራ እድል የሚናቅ ባለመሆኑ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ለማድረግ ወጥ የሆነ ሀገራዊ  ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን አመልክተዋል። ሆኖም ግን በቅሚያና ሌሎች ወንጀሎች ተሰማርተው የሚገኙ ሞተር ብስክሌቶች በመደበኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ተገቢው ቅጣት እንዲያገኙ ፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል ። ”በእኔ ምክንያት መሞት ይቁም” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሔደው የእግር ጉዞና የምክክር  መድረክ  የኃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ብዘት ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም