ምሩቃን ተማሪዎች ለሀገራዊ ልማትና ሰላም ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል... አቶ አወል አርባ

72
ሰኔ 30/2011 ምሩቃን ተማሪዎች የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትንና የሥራ ትጋትን በማጎልበት ለሀገራዊ ልማትና ሰላም ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ተናገሩ። የጎንደር፣ የወልዲያ እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠኗቸውን ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስምርቀዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሀ ግብር ያስተማራቸውን 8 ሺህ 365 ተማሪዎች ትናንት ያስመረቀ ሲሆን ተማሪዎቹ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 3ሺህ 200 ሴቶች ሲሆኑ ሦስት ተማሪዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ዘርፍ በ3ተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ በትምህርት ዘመናቸው ውጣ ውረዱን አልፈው ለውጤት እንደበቁ ሁሉ በስራው ዓለምና በማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውም መድገም ይኖርባቸዋል፡፡ ከሥራ ትጋት ባለፈ የሀገር ፍቅር ስሜትን በመያዝና ከሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር አንድነትን በማጠንከር አገር እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ልዩነታችንን በማክበርና የጋራ የሆኑ እሴቶቻችንን በመጠበቅ ታላቅ የነበረች ሀገራችንን ዳግም ወደ ታላቅነቷ መመለስ ይገባል” ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም በቀጣይ በራሳቸው ጥረትና ከሌሎች ጋር በአንድነት በሚያደርጉት ጉዞ ስኬትን ማስመዝገብ እንደሚችሉ አውቀው ሥራንም ሆን ውጤታማነትን ከሌላ መጠበቅ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው እጩ ምሩቃን በተቋሙ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሥራው ዓለም ተግባራዊ በማድረግ ሀገሪቱንና ማህበረሰቡን መጥቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ47 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል። በተመሳሳይ ዜና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 28 ተማሪዎች ዛሬ አስምርቋል፡፡ በመደበኛና በማታ የትምህርት መርሀ ግብሮች ሰልጥነው ከተመረቁት መካከል 1 ሺህ 700 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ከዕለቱ ምሩቃንም 700 የሚሆኑት በ2ኛ ዲግሪ የሰለጠኑ መሆናቸው ታውቋል። ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በምረቃው ላይ እንዳሉት ተቋማቸው በየጊዜው በርካታ ተማሪዎችን በማስመረቅ ሃገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ይግኛል፡፡ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢና የፌድሪ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው ተመራቂዎች የመንግስት ሥራ ሳይጠብቁ ስራ ፈጣሪ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በተመሳሳይ ዜና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 660 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ ሞላ በምረቃው ላይ ሀገሪቱን በልማት ወደፊት ለማምጣት የሰለጠነ የሰው ኃይል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግስትና ባለሀብቱ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሳደግ የሰለጠነውን የሰው ኃይል በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ነው የገለጹት። “ተማሪዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ከመስራት ባለፈ ምክንያታዊ መሆን፣ ከስሜታዊነት የጸዱ፣ ዘረኝነትንና ጎጠኛነትን የሚጠየፉ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀው የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ሳይጨምር እስካሁን ድረስ ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ ታውቋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎቹ የዕለቱ ተመራቂዎች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልግል በቁርጠኝነት ይሰራሉ። በሀገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሸረሸረ የመጣውን አንድነትና ፍቅር ለመመለስና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አንደሚወጠም ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም