ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስመረቀ

145
ሰኔ 30/2011(ኢዜአ) ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸው 2 ሺህ 107 ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ትናንት  ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 101  በሁለተኛ  የዲግሪ መረሀ ግብር የተማሩ ናቸው። በምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አመራር አባል  ዶክተር አብዲቃድር ኢማን ባስተላለፉት መልዕክት "ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በንድፍ ሀሳብና በተግባር የቀሰሙትን እውቀት ለህብረተሰብ ለውጥ እና እድገት ማዋል ይጠብቅባቸዋል" ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ኢልያስ ኡመር በበኩላቸው ተቋሙ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ች በመሃንዲስና፣ በጤና ሳይንስ ፣በግብርና፣ በህክምናና በሌሎችም የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው መሆኑን አስረድተዋል። ዩኒቨርስቲው ከመደበኛው ስራው ሳይወሰን በክልሉ ሰባት ከተሞች ማዕከላትን ከፍቶ ለማህበረሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና አስተዳደር ተመራቂ ወጣት አብዲ መሀመድ በሰጠው አስተያየት ከዩኒቨርስቲው በቀሰመው  እውቀት  ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ስራ ለመፍጠር  ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል። ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ከ24ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው  ስነስርዓት ወቅት ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም