ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 2ሺህ 880 ተማሪዎችን አስመረቀ

67
ሰኔ 30/2011(ኢዜአ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 880 ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው በምረቃ ስነስርአት ላይ በጥበብና በሰብአዊ ተግባራት አርአያ ናቸው ላላቸው ሁለት ሰዎችም የክብር ዶክተሬት ሰጥቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ አስተምሮ ካስመረቃቸው መካከል 63ቱ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ አረጋዊያንን በመደገፍና በመጦር ተግባር ለተሰማሩት ለወ/ሮ አሰገደች አስፋውና ለታዋቂው ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ የክብር ዶክተሬት ሰጥቷል፡፡ በምረቃው ላይ በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁ ተማሪዎች የተዘጋጁትን የወርቅ መዳሊያና የዋንጫ ሽልማቶች የሰጡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው፡፡ አቶ ፍቃዱ  በምረቃው ላይ እንዳሉት ሀገሪቱን ወደ ቀድሞ የስልጣኔና የዕድገት ማማ ለማድረስ ቁልፍ ሚና ላለው የትምህርት መስክ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ  በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይም የትምህርትና የስልጠና ዘርፍ ጥራትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መደረጉን  ነው የተናገሩት፡፡ ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀት ስራን ሳይንቁና ሳይጠብቁ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በቁርጠኝነት ሌት ተቀን እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ተማሪዎች ብዝሃነትን በማክበር በቀሰሙት ዕውቀት ለሀገር ዕድገት፣ ለሰላምና አንድነት ኃላፊነታቸውን  እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት በ6 ኮሌጆች፤ በ41 የትምህርት መስክ ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም