በሲዳማ ዞን የፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ ነው

98
ሀዋሳ ሰኔ 30/2011 (ኢዜአ) ከአካባቢ ጥበቃ ስራ ጎን ለጎን የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ስራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ አስታወቀ። ኤጀንሲው ከሲዳማ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያና ከይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪያል ፓርክ ጋር በመተባበር በዳሌ ወረዳ የችግኝ ተከላ አካሄዷል። በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑረዲን መሀመድ በችግኝ ተከላው ወቅት እንዳሉት ኤጀንሲው በግብርናው መስክ ለውጥ ለማምጣት እያከናወነ ያለውን ተግባር በአካባቢ ጥበቃው መስክም የሚጠበቅበትን ለመወጣት እየሰራ ነው። የኤጀንሲው ሰራተኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እያንዳንዳቸው አርባ ችግኝ እንዲተክሉ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ከአካባቢ ጥበቃ ስራው ጎን ለጎን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች እየተከሉ መሆኑን ገልጸዋል። ትናንት በተካሔደው  የተከላ ስነስርዓት በይርጋለም እየተገነባ ላለው የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪያል ፓርክ ግብዓት የሚሆን ሀስ የተሰኘውን የአቦካዶ ችግኝ በአርሶ አደር ማሳ ላይ እንዲተከል መደረጉን ተናግረዋል። ኤጀንሲው የአርሶ አደሩን የፍራፍሬ ችግኝ ፍላጎት በማየት በሲዳማ ዞን አንድ የፍራፍሬ ችግኝ ማዘጋጃ ጣቢያ ማቋቁሙን አመልክተው በቀጣይ በተለያዩ ወረዳዎች ንዑስ ጣቢያዎችን በማቋቋም ለአርሶ አደሩ በአቅራቢያው ችግኝ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የሲዳማ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ለጣ የታሞ በበኩላቸው "በዞኑ ያለውን የአየር ንብረት መሰረት ባደረገ መልኩ በቆላማና ደጋማ አካባቢዎች ከ37 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከላ እየተካሄደ ነው "ብለዋል። ከ1 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በመለየት ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በዞኑ እየተካሄደ ባለው የችግኝ ተከላ ስራ ከተዘጋጀት ችግኞች ውስጥ አንድ ሰው 40 ችግኝ እንዲተክል በተያዘው ዕቅድ መሰረት እስከ አሁን ድረስ 21 ሚሊዮን  መተከሉን ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል ጠቀሜታ ካላቸው ዋንዛ ፣ ቀረሮና  ሌሎች ሀገር በቀል ዝርያዎች በተጨማሪ ለተከላ ከተዘጋጀው 37 ሚሊዮን ችግኝ መካከል በ705 ሔክታር መሬት ላይ የሚተከል የአቦካዶና ማንጎ ችግኝ እንደሚገኝበት አስታውቀዋል። በዞኑ ለአቦካዶ አመቺ በሆኑ አካባቢዎች አንድ አርሶ አደር ከ500 እስከ 1 ሺህ ችግኝ እንዲተክል ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በኢንደስትሪያል ፓርኮች ኮርፖሬሽን የህብረተሰብ መልሶ ማቋቋም ዳይሬክቶሬት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ጴጥሮስ ማርቆስ እንደገለጹት ደግሞ የፓርኩ ስራ ሲጀምር የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት አቦካዶ በማቀነባበር ስራ ለመሰማራት አንድ ባለሀብት 32 ሺህ አርሶ አደሮችን በመመልመል ትስስር የመፍጠር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉ ውስጥ  ወይዘሮ ታፈሰች ወልዴ በሰጡት አስተያየት  አንድ ሰው አርባ ችግኝ እንዲተክል የተላለፈው መልዕክት በመደገፍ  ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከአርባ በላይ ችግኞችን እንደተከሉ ተናግረዋል። የዛሬው የተከላ ስራ ግን ለየት የሚያደርገው ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለምግብነት የሚውል አቦካዶ መትከል መቻላቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል። አርሶ አደር ባልቻ ገነሞ በበኩላቸው ምርት መስጠት ያቆመና ያረጀ ቡና በመንቀል ከሁለት ዓመት በፊት አቦካዶ መትከል እንደጀመሩ አስታውሰው በተያዘው ዓመት አምስት መቶ ችግኝ ለመትከል ጉድጓድ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ከይርጋለም  የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪያል ፓርክና ከሲዳማ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ጋር በመተባበር ትናንት የተከሉት የአቦካዶ ችግኞች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚጀምሩ ናቸው ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም