በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አዲስ አበባ ፖሊስ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል

79
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2011በአራተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አዲስ አበባ ፖሊስ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ከሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ 55 ወንድ እና 14 ሴት ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም የክብደት ዘርፎች ፉክክር ተደርጎባቸዋል። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጎንደር ከተማ የቦክስ ስፖርት ክለቦች በውድድሩ ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዛሬ በተጠናቀቀው ውድድር አዲስ አበባ ፖሊስ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። በድሬዳዋ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ደሴ እና አዲስ አበባ በተካሄዱት የ2011 ዓ.ም አራቱ ብሔራዊ የቦክስ ክለብ ውድድሮች ውጤት ተደምሮ በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ የዓመቱ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የዘንድሮው ውድድር ዋና አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና የሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ እንደሆነ አስታውሰዋል። በዚሁ መሰረት በድሬዳዋ፣ ወላይታ ሶዶና ደሴ ከተሞች በተካሄዱ ውድድሮች 11 ወንድ እና ሁለት ሴት በድምሩ 13 የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞች ተመርጠው ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ልምምድ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በአዲስ አበባው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ብቃታቸው ታይቶና ተገምግሞ በቦክስ ብሔራዊ ቡድኑ መካተት ያለባቸው ስፖርተኞች ካሉ ለመለየት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ከነገ በስቲያ ስብሰባ አድርጎ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተናግረዋል። በስብሰባው ላይ በሚተላለፈው ውሳኔ መሰረት የሚለዩ ስፖርተኞች ካሉ ከሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ቀደም ብለው ከተመረጡት ስፖርተኞች ጋር ተቀላቅለው ልምምድ መስራት እንደሚጀምሩ ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት። ውድድሩ ለክለቦች የውድድር አማራጭ ከማስፋት እና ተወዳዳሪዎች አቋማቸውን እንዲፈትሹ ከማድረግ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል። የዛሬው እና የዓመቱ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል። በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በደሴ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛ የብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን፣ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ ክለቦች አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም