በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሰማራት የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ተመራቂ ተማሪዎች

84
ሰኔ  29/2011 በመጪው ክረምት በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ። ዩኒቨርስቲው ዛሬ በካሄደው የምርቃ ሥነ ስርዓት ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አስመርቋል። ተመራቂ ተማሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት፤ በተለያዩ መስኮች በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው። ከዩኒቨርሲቲው በስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር የትምህርት መስክ የተመረቀው ተማሪ ሱራፍኤል ተክሌ በትምህርት ቆይታው ዕውቀት ከመገብየት ባሻገር አረጋዊያንና ህጻናት በመርዳት እንዳሳለፈ ገልጿል። በቀጣይም በደም ልገሳና በችግኝ ተከላ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የመሳተፍ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። ሌላዋ ተመራቂ ወጣት የምስራች አዳነ በበኩሏ ''በጎ ፍቃድ ላይ መሳተፍ ከተማረ ብቻም ሳይሆን ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው'' ያለች ሲሆን ሁሉም በሚችለው ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢሰጥ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ እምነቷን ገልጻለች። ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በመሆንም ደም በመለገስ የዜግነት ግዴታዋን ለመወጣት መዘጋጀቷን አስታውቃለች። ከፊዚክስ የትምህርት ክፍል የዲግሪ ተመራቂ የሆነው አደላሁ ኃይሉ በተለይ በፊዚክስና በሂሳብ የትምህርት ዓይነቶች ተማሪዎችን በማስጠናት ቀጣዩን ክረምት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚያውለው ጠቁሟል። ''በምችለው አቅም ማንኛውንም ተማሪ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ'' ሲል ለኢዜአ አስተያየቱን ሰጥቷል። በበጎ ፈቃድ ዋናው ከውስጥ እራስን አሳምኖ ሲሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የገለጸው ተመራቂ አደላሁ መንግሥትም በየዓመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጥ የማበረታታት ስራውን እንዲያጠናክርም ጠይቋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በ2011/2012 ዓ.ም 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች እንደሚሳተፉ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 22 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተወጠነው አገልግሎቱ በጎ ፈቃደኞች 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት እንደሚሰጡ ነው የተጠቀሰው። በዚህም መሰረት በክረምቱ በ13 ዋና ዋና መስኮች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳ፣ ጤና፣ ችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም