በሰሜን ሸዋ ዞን በመኸር አዝመራ በ21 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ለማልማት እየተሰራ ነው

93
ደብረብርሃን ሰኔ 29/2011 በሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮው የመኸር አዝመራ በኩታ ገጠምና በመደበኛ እርሻ በ21 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሩ በኢኮኖሚ አዋጭ በሆኑ ሰብሎች ላይ በልዩ ሁኔታ እንዲሳተፍና ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ በተለይም የቢራ ገብስ አርሶ አደሩን በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከብቅል ፋብሪካዎች ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አበበ እንዳሉት በዘንድሮው የመኽር አዝመራ ከሚለማው 21 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ። በተመረጡ 14 ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው የቢራ ገብስ ልማት 28 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውንም ቡድን መሪው ተናግረዋል ። ከልማቱም ለብቅል ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን ከ482 ሺህኩንታል በላይ የገብስ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የጠቀሱት፡፡ የአጎለላና ጠራ ወረዳ ጨፋና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሸናፊ ውቤ በሰጡት አስተያየት በቢራ ገብስ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ። ባለፈው ዓመት ባከናወኑት የቢራ ገብስ ልማት 25 ኩንታል ምርት በማግኘት ከ40 ሺህ ብር በላይ ሽጠው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ በመከተል 1 ሄክታር ተኩል መሬት በዘር መሸፈናቸውንና የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተጉ መሆናቸውን ገልፀዋል ። የዓሣ ባህር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቄስ ሙልየ ፍቃደ በበኩላቸው በቢራ ገብስ ልማት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሳተፉ ሲሆን በዚህ ዓመትም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም ወደ ልማቱ ሥራ እንደገቡ አስረድተዋል። በዞኑ ባለፈው ዓመት የመኽር ወቅት በቢራ ገብስ ዘር ከተሸፈነው መሬት 123 ሺህ 590 ኩንታል ምርት ተሰብስቦ እንደነበር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም