ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ባደረገው እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው- የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር

1545

አዳማ ሰኔ 3/2010 ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያደረገው እንቅስቃሴ ያጋጠሙትን ፈተናዎች  በማለፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለፁ።

የኦህዴድ ስምንተኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ ተጀምሯል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት  ድርጅቱ የህዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ጥያቄዎች ለመመለስ ባደረገው እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በቀጣይም የድርጅቱን ውስጣዊ አሰራር በመፈተሽ በጥልቅ ተህድሶ የተገኙ ተስፋ ሰጪ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

”ኮንፈረንሱ የእስካሁኑ የለውጥ ጉዞ የሚፈተሽበትና አመርቂ ውጤቶችን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው” ብለዋል።

”በኮንፈረንሱ ድርጅቱ አሁን ያለበትን ደረጃ በመፈተሽ የህዝቡ የለውጥና የዴሞክራሲ ጥያቄ  ምላሽ እንዲያገኝ ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም የህዝቦችን የለውጥ ፍላጎት በተቀናጀ መልኩ መምራት የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበትም  ተናግረዋል፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ  ”የአፍራሽ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ በሁሉም መስኮች እየተገኙ ያሉ ተስፋ ሰጪ ድሎችን በጠንከራ መሰረት ላይ ማኖር አለብን” ብለዋል።

ቀደም ሲል በየደረጃው በተካሄዱ ኮንፈረንሶች የተዛነፈ አመለካከትና አሰተሳሰብ በግልፅ ተፈትሾ መውጣቱን ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ ከወረዳ እሰከ ክልል ድረስ ድርጅቱ ውስጣዊ አሰራርና የትግል አቅጣጫዎችን የሚፈትኑ ግለኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና አደርባይነትን  ለማስወገድ ግምገማ ማካሄዱንም ተናግረዋል፡፡

ግምገማውን ተከትሎም 1ሺህ 500 የአመራር አባላት ከስልጣናቸው የተነሱ  ሲሆን 540 የሚሆኑት ደግሞ ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተደርገዋል።

በድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አባላት፣ አመራሮችና ደጋፊዎች ተሳትፊ ሆነዋል።

ኮንፈረንሱ እስከ ሰኔ 5 ቀን 2010 እንደሚቆይም ከወጣው መረሃ ግብር መረዳት ተችሏል።