በስድስት አመታት ውስጥ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገችው አየርላንድ ድጋፏን እንደምትቀጥል ገለጸች

64
ሰኔ 28/2011  ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገችው አየርላንድ ዘርፈ ብዙ የልማት ድጋፏን እንደምትቀጥል ገለጸች። አገሪቱ እአአ ከ2014 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስታከናውናቸው የነበሩ የልማት ድጋፎችን በተለይም በማህበራዊ ጥበቃ በሰብዓዊ መብት መስኮች ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች። በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ሶንጃ ሂላንድ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት አጋርነት በዓለም ላይ ካላት አጋርነት ቀዳሚው ነው። አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የላቀ አጋርነት እንዳላት አምባሳደሯ ጠቁመዋል። የሁለቱ አገሮች ዋና ዋና ትብብር መስኮች ማህበራዊ ዋስትና በተለይም ልማታዊ ሴፍቲኔ መርሃ ግብር የእናቶች ህጻናት ጤና፣ መልካም አስተዳደር፣ ስርዓተ ጾታ፣ እንዲሁም የግብርና ስራዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል። ''በአሁኑ ወቅት ከስድስት ዓመታት በፊት የጀመርነውን የልማት ስትራተጂክ ዕቅድ የምናጠቃልልበት ምዕራፍ ላይ እየደረስን ነው፤ በልማት ትብብር ሂደቱ አምስት ቢሊዮን ብር ወይም 160 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ መዋዕለ ንዋይ ፈሷል'' ብለዋል። አምባሳደሯ። በአየርላንድ መንግስት፣ በዓለም ዓቀፍ ለጋሾችና በኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ጥረት የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉንም አምባሳደሯ ገልጸዋል። ባለፉት 15 ዓመታት የእናቶች ሞትን በመቀነስ ረገድ አመርቂ ስራ መሰራቱን እንደተገነዘቡ የገለጹት አምባሳደሯ፤ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ''እናቶች ስንት ልጅ መውለድ እንዳለባቸው የመወሰን ሃላፊነት እንዲኖራቸው፣ የቅድመ ወሊድ የድህረ ወሊድ ክትትል የማግኘት መብት እና ጤናማ ልጅ ወልዶ የማሳደግ ሃላፊነትን እናቶች እንዲያገኙ በማስቻል በኩል የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው'' በማለት በዘርፉ የተሰራውን ስራ አድንቀዋል። አየርላንድ በኢትዮጵያ የመጣውን ፖለቲካዊ ናኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደምትደግፍ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ለማገዝ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ አጠላይ የፖለቲካ ሁኔታ ምቹ ሆኖ ምህዳሩ ሰፍቶና ዴሞክራሲያዊነቱ እየተጠናከረ ስለሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርዱን በመደገፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካካሪ ሆነው ነጻ፣ ገለልተኛና ግልጽ የሆነ ምርጫ እንዲያካሂዱ ድጋፋችንን እናደርጋለን'' ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የስራ አስፈሚው ተጠያቂነት እንዲጠናከር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አየርላንድ በአቅም ግንባታ መስክ ድጋፍ እንምታደርግ ተናግረዋል። የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ጥር ወር ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ፍሬያማ ውይይቶችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ማካሄዳቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም