ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ የአፍራሽ ኃይሎችን ሴራ በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

70
ሰኔ 28/2011 በአዳማ ከተማና በኦሮሚያ ክልል አስተማማኝ ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡ የለውጡ እንቅፋቶች አፍራሽ ሴራ በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ  ተጠየቁ። የአዳማ ከተማና አካባቢዋ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ "አንድነታችንን ጠብቀን ያገኘነውን ድል ወደ ላቀ ምዕራፍ እናሻግራለን" በሚል መሪቃል ዛሬ ተካሂዷል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው በእዚህ ወቅት እንደገለጹት በከተማዋም ሆነ በክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ መስራት ይኖርበታል። በእዚህም የከተማዋና አካባቢዋ ሕብረተሰብ የለውጡ እንቅፋቶች የሚፈጥሩትን አፍራሽ ሴራ በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ነው የጠየቁት። "የኦሮሞ ህዝብ እንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልገው አሁን ነው" ያሉት ከንቲባው፣ ህዝቡ በከተማዋም ሆነ በክልሉ ከሚኖሩት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያለውን አብሮነት ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል። በፖለቲካ የተገኘውን ውጤት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመድገምና የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና በልማቱ መረባረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። "መንግስት ለውጡን ለመቀልበስ እየጣሩ ያሉ ኃይሎችን ከጥፋታቸው ለመከላከል ጠንክሮ እንደሚሰራ አቶ አሰግድ ገልጸው፣ በፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ህዝቡን በማተራመስ የራስን ዓላማና ፍላጎት ማስፈፀም እንደማይቻል አስረድተዋል። በተለያዩ ጊዜያት የኦሮሞ ህዝብ ማንነት፣ ባህልና ቋንቋው እንዳይስፋፋ ሲደረግ እንደነበር ጠቁመው ክህዝቡ አብራክ የወጡ የቁርጥ ቀን ልጆች ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ በማስተባበርና ከሌሎች የሀገሪቱ ህዘቦች ጋር በከፈሉት መሰዋዕትነት የዛሬው ድል መገኘቱን ተናግረዋል። ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ቡድኖች ጥቅማቸው ከተነካባቸው ኃይሎች ጋር በመሆን የነበረውን የግፍ አገዛዝ ለመመለስ እየተፍጨረጨሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሰግድ ይህን ተግባር ለማክሰም በክልሉ መንግስት በኩል ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል። በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ላይ የተፈፀመው ጥቃት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጭምር የተቃጣ ድርጊትና በቀጣይ የጥፋት ኃይሎችን ለመታገል በር የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል። "የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ግለሰቦችን በገንዘብና በጦር መሳሪያ ጭምር ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ባለሃብቶች መኖራቸውን የክልሉ መንግስት ደርሶባቸዋል" ብለዋል። በክልሉ ሀብት አፍርተው እየኖሩ ያሉ ባለሃብቶች ሀብታቸውን ለሀገር ልማት ማዋል እንጂ ጽንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖችን መደጎም ፈፅሞ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው "በዚህ ተግባር የተሳተፉትን በመለየት በቅርቡ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል። የኦሮሞ ህዝብ በሆደሰፊነትና በትግዕስት ከመሪ ድርጅቱና ከመንግስት ጎን በመሆን ለውጡን ከዳር ለማድረስ መረባረብ እንዳለበት አስገዝበዋል። "የኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ በመደማመጥ እንድነቱን ጠብቆ በትግሉ ያገኘውን ድል ለውጤት እንዲበቃ ከድርጅታችንና መንግስታችን ጎን እንቆማለን " ያሉት ደግሞ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ አቶ ሙሐመድ ሁሴን ናቸው። ህግ ወጥ የጦር መሳሪያ በማዘዋወርና አፍራሽ ኃይሎችን በቁሳቁስና በገንዘብ የሚደግፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት በትኩረት  መስራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የጨፌ ቀበሌ ነዋሪና የመድረኩ ተሳተፊ አቶ ሚሊዮን አብዲ ናቸው። "የጦር መሳሪያ ዝውውር በከተዋም ሆነ በሀገሪቱ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ያደርጋል" ያሉት አቶ ሚሊዮን በአጎራባች ክልሎች ወሰን ላይ በሚፈጠሩ ግጭት የሰው ህይወት እየጠፋ ያለው በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በመሆኑ መንግስት ጥብቅ ክተትለ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ዛሬ በተካሄደው የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ላይ ከአዳማና አካባቢዋ የተወጣጡ 1ሺህ 500 ነዋሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም