በአዲስ አበባ እምብርት የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በተማሪ እጦት ተቸግረዋል

217
ሰኔ28/2011በመሃል አዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኞቹ የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚፈለገው መጠን ተማሪዎችን ባለማግኘታቸው በአንድ ክፍል እስከ 10 ተማሪዎች ለማስተማር እየተገደዱ እንደሆነ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፤ የመንግስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአቅማቸው ልክ ተማሪ ባለማግኘታቸው ውስን ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በመቀበል ከአቅም በታች እየሰሩ ይገኛሉ። በመንግስት ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል 50 ተማሪዎች መማር እንደሚችሉ መመሪያው ቢፈቅድም በ2011 የትምህርት ዘመን አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በአንድ ከፍል ከ12 የማይበልጡ ተማሪዎችን አስተምረው ማጠናቀቃቸው ታውቋል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ፤ የትምህርት ጥራት፣ መልሶ ማልማትና የአመለካካት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት በመንግስት ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል። በዚሁ ምክንያት መንግስት ለመማር ማስተማሩ ስራ ያስገነባቸው የመማሪያ ክፍሎች፣ መሳሪያዎችና መሰረተ ልማቶች እንዲሁም ለትምህርት ዘመኑ የተያዘው በጀት ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉን ኢዜአ በትምህርት ቤቶቹ ባደረገው ምልከታ ታዝቧል። ትምህርት ቤቶቹ በአንድ ክፍል ውስጥ ማስተማር ካለባቸው ተማሪዎች ከግማሽ በታች ብቻ በማስተማር የመማሪያ ቁሳቁሶችና የሰው ሃይል ያለ አግባብ እየባከነ መሆኑን የወላጅ፣ ተማሪና መምህራን ጥምረት (ወተመ) እንዲሁም የትምህርት ቤት ሃላፊዎች ተናግረዋል። የተማሪ ቁጥር መቀነስ የሚታይባቸው ከዚህ ቀደም በርካታ ተማሪ የሚያስተናግዱ የአራዳ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስና የልደታ ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ ትምህርት ቤት እንደነበሩ ነው የተናገሩት። የወላጅ ተማሪ መምህራን ጥምረት አቶ ምስጉን ተፈራ እንዳሉት፤ አብዛኛው ወላጅ በመንግስት ትምህርት ቤት ልጆቹን ለማስተማር ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ እየሆነ መጥቷል። የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከክፍያ ነጻ ቢሆኑም ከትምህርት ጥራትና ከሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሄ ስለማይሰጣቸው ወላጅ ተቸግሮም ቢሆን በግል ትምህርት ቤት ለማስተማር እየተገደደ እንደመጣ አስረድተዋል። የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ጥራት፣ ከመምህራን አቅም ማነስ፣ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ከወላጆች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎታቸው አነስተኛ መሆኑንም ያነሳሉ። አብዛኛው የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቁጥር ማነስ በመልሶ ማልማት እንደሆነ ቢታሰብም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ለሚነሳ ጥያቄዎች ለተማሪዎች ቁጥር መቀነስ ዋነኛው መሆኑን የተናገሩት አቶ ምስጉን ናቸው። ከዚህ ቀደም የህዝብ ትምህርት ቤት ሆነው አሁን በመንግስት የተዘዋወሩ የተማሪዎች በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ የረዥም ጊዜ እቅድ ተይዞ ስለማይገነቡ መንግስትን አላስፈለጊ ለሆነ ወጪ ሲዳርጉት እንደሚታዩ ገልጸዋል። እዛው አጎራባች ያሉ የትምህርት ብልጭታ፣ ራስ አበበና ሌሎችም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪ እጦት ሲቸገሩ ኒውኤራና ቤተልሄም የተባሉ ትምህርት ቤቶች  በርካታ ተማሪዎችን ያስተናግዳሉ። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤልያስ ገብረየሱስ እንዳሉት፤ በመሃል አዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ከመማር ማስተማሩ ጋር ያሉ ተዛማጅ  ችግሮችን የሚፈታ ጥናት እየተደረገ ነው። ከበጀትና ከሌሎች የመምህራንን ድልድል ጋር ተያይዞ አዲስ መዋቅር ተሰርቶ ወደ ስራ ተገብቷል ይሄ ችግር በዚህ ይፈታል ብለዋል። በአንድ ክፍል የተማሪዎች ቁጥር ማነስ መማር ማስተማሩና ለትምህርት ጥራቱ ከፍተኛ እገዛ ስለሚያደርግ ይህ እንደ ችግር ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚ መምህራን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ከ225 በላይ የመንግስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም