አርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታን በመጠቀም ምርታማነቱ እንዲጨምር ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል

253
ሰኔ28/2011 በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የገጠር መሬት መጠቀም መብት ማረጋገጫ ካርታ ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ መንግስት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተገለፀ።
የገጠር መሬት አዋጅን ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ በመዘግየቱ ቀደም ብሎ ካርታ የተሰጣቸው አርሶ አደሮች ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደለም ተብሏል። የገጠር መሬት የመጠቀም መብት ማረጋገጫ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር አርሶ አደሩ ከግብርና ውጭ በሆኑ የምጣኔ ኃብት ዘርፎች በመሰማራት  ህይወቱን  ለማሻሻል  እንደሚያስችለው ባለሙያዎች ይገልፃሉ።ሆኖም  እስካሁን  ባለው  ሁኔታ  በኢትዮጰያ  ካሉ ከ50 ሚሊዮን የሚልቁማሳዎች የመሬት መጠቀም   ካርታ የተሰጣቸው 15 ሚሊዮን ያህሎቹ ብቻ መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስቴር  የተገኘው  መረጃ  ያመለክታል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ የእኔነት ስሜት ስለማይሰማው መሬቱን ለመንከባከብ ያለው ተነሳሽነትና ባለው በመሬት ሃብት ላይ የሚገኘው ጥቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ከዝናብ ጥገኝነት ሳይላቀቅ ቆይቷል። መንግስት ይህንን  ችግር  ለማቃለል ከ10 ዓመት  ጀምሮ  አርሶ  አደሩ የገጠር መሬት  የመጠቀም  መብቱን የሚያረጋግጥለትን  ካርታ  እንዲያገኝና  በመሬቱ  የተሻለ  ተጠቃሚ  እንዲሆን ሰፊ  ተግባራትን  እያናወነ  ይገኛል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል ከእንግሊዝ ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ጋር በመተባበር የሚተገበረውና 'ሊፍት' በሚል ምህፃረ ቃል የሚጠራው ፕሮግራም ይጠቀሳል። ከእንግሊዝ መንግስት በተመደበ 72 ሚሊዮን ፓወንድ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት እየተተገበረ ባለው ፕሮግራምመሰረትም ከ12 ሚሊዮን የሚልቁ አርሶ አደሮች  በያዙት መሬት  የመጠቀም  መብት የሚያጎናፅፋቸውን የባለቤትነት ካርታ ማግኘታቸውን የፕሮግራሙ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መንበሩ አለማየሁ ለኢዜአ ገልፀዋል። በዚህም አርሶ አደሩ  መሬቱን  በፈለገው  መንገድ  ከማልማት  ባሻገር  የመሬቱን  ካርታ አስይዞ  የመበደር፣ መሬቱን የማከራየትና የማውረስ መብቶች ይኖሩታል። ይህም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ህይወትበዘላቂነት ለማሻሻል ዓይነተኛ ሚና ያለውመሆኑንም ተናግረዋል። ሆኖም ካርታውን ያገኙ አርሶ አደሮች በተሰጣቸው ካርታ የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አይደለም ብለዋል። ለዚህም ምክንያቱ የገጠር መሬት የመጠቀ ምካርታን አስይዞ የመበደር፣ የማከራየትና የማውረስ መብቶችን ህጋዊ ለማድረግ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ ያለውን የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ በመዘግየቱ መሆኑን አክለዋል። እርሳቸው እንደሚሉት አዋጁን ለማሻሻል የተጀመረው ተግባር እስካሁን ተጠናቆ አዋጁ ሥራ ላይ አልዋለም። ለአርሶ አደሩ መሬቱን በዋስትና አስይዞ የመጠቀም መብቱን ማረጋገጥ ይችል ዘንድ አዋጁን የማሻሻል ሥራ የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፤ ሆኖም እስካሁን ወደተግባር አልተገባም። የቀድሞው  የገጠር መሬት አስተዳዳር አዋጅ 456/97 አርሶ አደሩ መሬትን በዋስትና አስይዞ መበደር ይችላል የሚል አንቀጽ የለም፤ የመጠቀም  መብታቸውን አስይዘው መበደር የሚችሉት ኢንቨስተሮች ናቸው። አዋጁ አርሶ አደሩ ካርታውን አስይዞ እንዲበደር በሚያስችል መልኩ ረቂቁ ተዘጋጅቷል ሲሉም አቶ መንበሩ ተናግረዋል። አንዳንድ ክልሎች የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት አርሶ አደሩ ካርታውን አስይዞ ብድር እንዲወስድና ምርትና  ምርታማነትን  እንዲጨምር  እያደረጉ ቢሆንም በአብዛኞቹ ክልሎች ግን ይህ እየሆነ አይደለም ይላሉ። በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አያያዝና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ ገብረመስቀል እንዳሉትአርሶ አደሩየገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታን አንዲያገኝ ከአጋር ድርጅቶች በተገኘ ከፍተኛ ድጋፍና መንግስት በመደበውበጀት ሰፊ ስራ ተስርቷል። አንዳንዳድ ክልሎች የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት 10 ሺህ አርሶ አደሮች ካርታቸውን አስይዘው ብድር እንዲወስዱበማድረግ ህወታቸውን እያሻሻሉ መሆኑን አመልክተዋል። አርሶ አደሩ ካርታውን አስይዞ የመበደር፣ የማከራየትና በሚፈልገው መጠን በመሬቱ በመጠቀም ህይወቱን የማሻሻል ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ነገር ግን ይህን ችግር ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀው አዋጅ የማሻሻል ሥራ መዘግየቱን ተናግረዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ረቂቁ ለመጨረሻ የህግ እይታ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ መላኩን ጠቁመዋል። ጉዳዩ ሰፊ ጊዜ የሚፈልግና በጥልቀት መታየት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎች በየጊዜው መለዋዋጥ ለመዘግየቱ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል። ይህን ስራ በቀጣይም ውጤታማ ለማድርግ የክልል ሃለፊዎችና ለሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ቁርጠኛአቋም ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም