የፋብሪካው ሰራተኞች 'የደሞዝ፣ የጤና አገልግሎትና የስራ ደህንነት ጥያቄችን' መልስ አላገኘም አሉ

101
ሰኔ 28/2011 በአፋር ክልል ሰመራ አካባቢ የሚገኘው ኤስ.ቪ.ኤስ የአይዎዳይዝድ ጨው ፋብሪካ ሰራተኞች 'ድርጅቱ የደሞዝ፣ የጤና አገልግሎትና የስራ ደህንንት ጥያቄችንን አልፈታልንም' አሉ። ፋብሪካው በበኩሉ ሰራተኞች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሂደት እንደሚፈታ ገልጿል። 'ኤስ.ቪ.ኤስ' የተሰኘው ፋብሪካ እ.ኤ.አ በ2016 በውጭና በአገር ወስጥ ባለሀብቶች በጋራ የተቋቋመ በኢትዮጵያ ብቸኛው አይዎዳይዝድ ጨው አምራች ፋብሪካ ነው። አሁን ላይ ፋብሪካው በቀን ከ12 ሺህ እስከ 15 ሺህ ከረጢት በአይዎዲን የበለጸገ ጨው እያመረተ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ሲሆን ከ900 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች  ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል። ወደስራ ከገባ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው ኤ.ቪ.ኤስ የአይዎዳይዝድ ጨው አምራች ፋብሪካ ሰራተኞች ፋብሪካው የስራ እድል ቢፈጥርም 'የሰራተኞችን ጥቅማ ጥቅምና ጤና ሁኔታ በተመለከተ ያነሳናቸው ጥያቄዎች አልተመለሱም፤ ቅሬታችንም አልተፈታም' ብለዋል። ለ24 ሰዓታት በፈረቃ የሚሰራው ፋብሪካ ሰራተኞቹ በቀን 75 ብር እንደሚከፈላቸው ገልጸው፤ ጥቅማ ጥቅም ከዓመት ዓመት ጭማሪ እንደሌለው ያብራራሉ። በሌላ በኩል በፋብሪካው ጉዳት የደፈረሰበት ሰራተኛ ዋስትና እንደሌለው አብራርተው፤ ከዚህ በፊት አንድ ሰራተኛ በአካሉ ላይ ጉዳት ደርሶበት የተደረገለት ነገር እንደሌለ ነው ያብራሩት። በስራ ቦታ ላይ የስራ ልብስ ወይም ሴፍቲ ካለመኖሩ በተጨማሪ የጤና ጣቢያ አገልግሎት እንደሌላቸውም አብራርተዋል። ስራ ላይ ያገኘናቸው አፍቲ አብደላ አሊና ሁጂብ አሊም 'የስራ ጫና አለ፤ የጤና አገልግሎት የለም፤ ለችግር ጊዜ ፈቃድ አይሰጥም፤ ለሶስት ዓመታት በ75 ብር እየሰራን ነው' ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል ናቸው። በፋብሪካው የሰራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር መሃመድ አብዱ ሰራተኞች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ለአብነትም የደሞዝ፣ የጤና አገልግሎት፣ የስራ ደህንነት አልባሳት ጥያቄዎች የሰራተኞች ጥያቄዎች መሆናቸውን አብራርተዋል። አዲስ ስራ አስኪያጅ መምጣቱን የገለፁት አቶ መሃመድ፤ ይህን ተከትሎ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም ምላሽ ያገኛሉ የተባሉት የሰራተኞች ጥያቄዎች ግን እስካሁን ምላሽ አላገኙም፤ መስተካከል አለባቸው ብለዋል። በፋብሪው የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታሰው ጸጋ ድርጅቱ በአይወዲን የበለጸገ ጨው አምርቶ ለገበያ ሲያቀርብ፣ በአይወዲን ያልበገለጸ ጨው ደግሞ ለቆዳ ፋብሪካዎች እንደሚያመርት ይገልጻሉ። እስካሁን ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ቢሆንም ወደፊት ለውጭ ገበያ ለማቅረብም እቅድ እንዳለው ገልጸው፤ ከስድስት ወራት ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም በህገ-ወጥ  መንገድ ገበያውን የሚይዙ የጨው ምርቶች ፋብሪካው ትርፋማ እንዳይሆን አድርገውት እንደነበር ገልጸል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በክልሉ መንግስት በተደረገለት ድጋፍና ክትትል በህገ-ወጭ  መንገድ እየወጡ ገበያውን ከተቆጣጣሩ በአይወዲን ያልበለጸጉ ምርቶችን ተወዳድሮ የተሻለ ደረጃ ላይ መሆኑን አመልክተዋል። የፋብሪካው ሰራተኞች የሚያነሷቸውን ከክፍያ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በተመለከተ ሰራተኛው ዝቅተኛውም ሆነ ከፍተኛ ተከፋዮች ጥያቄ እንደሚያነሱ ገልጸው ችግሮቹን በሂደት ለመቅረፍ እየሰራን ነው በለዋል። ከሰራተኛ የስራ ልብስ ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ጥያቄ ግን ስፍራው በርሃ ስለሆኑ ለሰራተኞች  የፋብሪካ አልባሳት ወይም ሴፍቲ ለብሰው ለመስራት የሙቀት አደጋ ስለሚያጋጥም አልተዘጋጀም ብለዋል።   የኢንዱስትሪ ስራ ሲሰራ ችግር ያጋጥማል ያሉት አቶ ጌታሰው፤ በሰራተኞች የሚነሱ ጥቄዎች ወደፊት መልስ ያገኛሉ ብለዋል። ከዚህ በፊት ጉዳት ደርሶበት የተጎዳ ሰራተኛን በተመለከተም በጤና ባለሙያዎች የተቀመጠለትን ተገቢ የአካል ጉዳት መጠን ካሳ ማግኘቱን ይገልጻሉ። አይወዳይዝድ ሳይሆኑ በህገ ወጥ መንገድ ወደገበያ የሚወጡ የጨው ምርቶች በህብረተሰቡ ላይ ከሚፈጥሩት የጤና እክል ባሻገር ፋብሪካው በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እያደረጉ በመሆኑ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም