የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርትና የመገናኛ ብዙሃን ዕይታ

60
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2011 በጀት አመት የመንግስታቸውን አመታዊ የስራ አፈጻጸም ለህዝብ እንድራሴዎች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በመሆኑም ባቀረቡት የመንግስታቸው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ መነሻ በማድረግ የተለያዩ የአገር ውስጥ እና የውጪ አገር መገናኛ ብዙሃን የሪፖርቱን ጠቅላላ ይዘትና የ2012 የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ብለው በዘረዘሯቸው መነሻ ዕቅዶች ዙሪያ በምን ዕይታ እንደዘገቡ እንደሚከተለው ዳሰውታል።

ከመገናኛ ብዙሃኑ መካከል የአማርኛው አምድ ቢቢሲ አንዱ ነበር። የወሬ ምንጩ ዘገባውን ሲጀምር  የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵን አንድነትና ሉአላዊነት የሚገዳደር ማንንም ግለሰብም ሆነ ቡደንን አንታገስም "በእስክሪብቶ ሳይሆን ክላሽ ተሸክመን ለመዋጋት ዝግጁ ነን” በማለት የገለጹበትን ሁኔታ በማውሳት አጠቃላይ የሪፖርታቸውን ዝርዝር ይዘት አይቷል። በዚህም ተሞክሮ ከሸፈ በተባለው “መፈንቅለ መንግስት” የተለያዩ የመንግስት ፈተናዎችን በመዘርዘር በፌደራል የመንግስት ተቋማት ላይ እየታየ ያለውን የብሄር ተዋጽዎ፣ የክልል እንሁን ጥያቄ፣ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች፣ እና በአጠቃላይ የኢኮኖሚውን እና የአገሪቷን የወደፊት እጣ ፈንታ በሚያሳይ መልኩ እንደነበር የሚል ሀሳብ በዘገባው ሰፍሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሪፖርት አጠቃላይ የመንግስታቸውን አፈጻጸም የሚያሳይ መሆኑንና የመጪው የመንግስት በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫ ያስቀመጡበት ሁኔታ በተለይ የወጣቶችን የስራ ዕድል ፈጠራ በማስፋፋት የስራ አጥ ቁጥርን መቀነስ የሚበረታታ እንደነበረም አውስቷል።

በሌላ ዜና ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የተሞከረውን የመፈንቅለ መንግስት ከአብራሩ በኋላ የአገሪቷን ሉአላዊነት ለመጠበቅ አንደራደርም፤ ከአስፈለገም “ከእስክብሪቶ ወጥተን መሳርያ ተሸክመን እንዋጋለን” ማለታቸውን በማውሳት የዘገበው ደግሞ አፍሪካ ኒውስ ነው። ከዚህ ጋር ተያየዞ በጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው የተባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የተለያዩ ግለሰቦችን የመያዙ ጉዳይ የተፎካካሪ ፓርቲወፖችን የሚያዳክም ነው ሲልም ወቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተው፤ በዚህም መሰረት ከሽብር ቡድን ጋር በተያያዘ 48፣ በተለያዩ ስፍራዎች ከተፈጸሙ ብሔርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች የተጠረጠሩ 799 አመራሮችና የፀጥታ ኃይል አባላት እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 34 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለምክር ቤቱ የገለጹበት መንገድ መንግስት ለህግ የበላይነት መከበር የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቆርጦ እንደተነሳ የሚያሳይ ነው በማለትም መገናኛ ብዙሃኑ ሀሳቡን ያትታል። አጠቃላይ የንግግራቸውን ይዘት በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፍ በመከፋፋል በተለይም ተጨማሪ የስራ ዕድል ፈጠራን በትኩረት ለመስራት የታሰበበትን ሁኔታ በአንክሮ መታየቱንም ዘገባው አውስቷል።

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ የተደረገውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በመጥቀስ ዘገባውን የጀመረ ሲሆን፤ በዚህ መፈንቅለ መንግሥት የተሳተፉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ፤ ከጥቂት ወራት በፊት ቤተ መንግሥት ከመጡ ወታደሮች አብዛኞቹ መሳተፋቸውንና በዚህም መከላከያ ገምግሞ አስሮ እነዚህ ወጣቶች ናቸው ይማራሉ ብሎ የሸኛቸው ነበሩ መባሉ የጸጥታ ዘርፉ ትኩረት እንደሚሻው በማስታወስ ይህ አይነት ክስተት ተመልሶ እንዳይመጣ ሊታሰብበት የሚገባ አገራዊ ጉዳይ እንደሆነም  አስድምሮበታል። ዘገባው አክሎም በጉዳዩ ዙሪያ  የሚካሄደው የምርመራ ውጤት ገና ባይወጣም፤ በአዲስ አበባ እና በባሕርዳር ሰኔ 15/2011ዓ.ም የተፈፀመው የፖለቲካ እና የወታደራዊ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ ተያያዥነት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸውን በመጥቀስ ሌላ ጉዳዩን የማጽዳት ተግባር እንደሚያስፈልግ የታየበት ክስተትም እንደሆነ  አትተዋል።

ከክልል እንሁን ጥያቄዎች ጋር በተየያዘ የጀርመኑ ዶቼ ቬለ በሃዋሳ ተገኝቶ ማህበረሰቡን በማነጋገር የሰራው ዘገባ እንደሚያሳየው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ክልላዊ መንግሥት ለማቆም ጥያቄ ስላቀረቡ ዞኖች የሰጡት ማብራሪያ ለአንዳንዶች ተገቢ ለሌሎች ኢ-ምክንያታዊ ከመሆኑም በላይ ጥያቄው መዘግየቱይ ተግባራዊ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል ሲሉ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲኣን) ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ ተናግረው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ሀይለ ቃል የታከለበት ንግግራቸው በፓርቲው አባላትና በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ክርክር አስነስቷል፤ ቅሬታም ፈጥሯል ሲሉ አብራርተዋል።

ሀላፊው አክለውም ጉዳዩን ከሱማሌ ክልል ጋር ያያያዙበት ሁኔታ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑና ሃዋሳ የተለያዩ ማህበረተሰቦች በአንድ ላይ የሚኖሩባት ትልቅ ከተማ ከመሆኗም በላይ፤ መሪዎችን ተቀብላ በሰላም ስታስተናግድ መኖሩዋን አስረድተው፤ ይህ ሆኖ እያለ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አምና ከተከሰተው ችግር ጋር አያይዘው ማንሳታቸው ተገቢ አይደለም በማለት ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የክልል እንሁን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል። ''በደቦ እና በጩኽት የሚመለስ ነገር ለማስተናገድ ከእንግዲህ ትዕግስታችን አልቋል። ሁሉም ሥርዓት ጠብቆ ይሄዳል፤ በሥርዓት እንመልሳልን። ያን የማይጠብቅ ከሆነ በተለመደው መንገድ እናስተናግደዋለን።" ማለታቸው ይታወሳል።

በሌላ ዜና የአሜሪካ ድምጽ አማርኛው ክፍል ቪኦኤ ያቀረቡት ሪፖርት አገሪቷ በህግና ደንብ የምትመራ እንደሆነች ያሳየበት ነው ሲሉ የገለጹት ደግሞ የኢዜማ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ናቸው። በተለይ ህገ መንግስታዊና ክልል እንሁን የሚል ጥያቄዎችን የመለሱበት መልስ አግባብነት ያለውና አገሪቷ እና ህዝቦቿ ወደ መረጋጋት የሚወስድ ነው ሲሉም አክለዋል። ይህም አካሄድ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባት አማራጭ የሌለው አካሄድ እንደሆነ እና ኢ መደበኛ የሆነ አካሄድ ከአሁን በኋላ ቦታ እንደማይሰጠው ያሳዩበት ገለጻ እንደሆነም አብራርተዋል።በመጨረሻም መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳየበት ሪፖርት ነበር ሲሉም ጠቅሰዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ሁለቱ አካሄዶች የሚጋጩ ቢሆንም ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻልና የማህበረሰቡን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ያደረገ መልስ እና የአገሪቱን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ትክክልኛ እና ተመዛዛኝ አካሄድ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነና ተስፋ የሚጣልበት አካሄድ ይሆናል ብለው እንደሚያሰቡም አስረድተዋል። በየቦታው እየተደረጉ ያሉት ህገወጥ አካሄዶች በየጊዜው እያደገና እና እየፈረጠመ የመጣ አካሄድ ነው ብለው እንደሚያስቡም አስረድተዋል። ከዚህ ጋር በተየያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት አመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አጠቃላይ የመንግስትን አካሄድ ከማሳየቱም በላይ  መንግስት በቁርጠኝነት የመስራት ዕቅድ እንደነበረ መረዳት ይቻላል።

በመጨረሻም ጸሃፍት መስከረም አበራ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ በሚል ፎረም ፎር ዴሞክራሲ ድረ ገጽ ላይ ባወጣችው ጽሁፏ እንዳስነበበችው፤ መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ከመገንዘብ በዘለለ በዕርሳቸው እና በመንግስታቸው ለሚደረገው ትችት አስተማሪነቱ መታየት እንዳለበት ትገልገጻለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይና መንግስታቸው ከለውጡ ማግስት ኢትዮጵያን በግልጽ ያየንባት መሆኑ ደግሞ በእሳቸው ልክም ባይሆን እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ማድረግ ካለበት በርካታ ነገሮች መካከል ህልውናን ማስጠበቅ ይገባል ሲትልም ታስረዳለች። ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ ሲትልም ታስረዳለች፡፡

በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም በማለትም ሀሳቧን ታስረዳለች፡፡

በተመሳሳይ ምንም እንኳን ነገሩ ስሜታዊ ሊያደርግ ቢችልም እንደ አገር መሪ ስሜታዊነት መቀነስ እንደሚገባም ታስረዳለች። ይህም ስሜታዊ መሆን ሁለት አደጋ እንዳለውም ትገልጻለች።  አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ፤ ሁለተኛው ደግሞ ተጠልቻለሁ የሚል ስጋት ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡ በመቀጠልም “አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣ የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል” ስትልም ታስረዳለች፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ከማድረጉም በላይ፣ ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ሊቀንስ ይችላል የምትለው ጸሃፊዋ፤ በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላልና መረጋጋቱ ይጠቅማል በማለትም  ሀሳቧን ሰጥታለች፡፡

   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም