የመንግስት ልማት ድርጅቶችንና ፕሮጀክቶችን ወደግል የማዛወር ሂደቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርጋል

57
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2011 የመንግስት የልማት ድርጅቶችንና ፕሮጀክቶችን ወደግል የማዛወር ሂደቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ እመርታ እንደሚያመጣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አንተነህ አለሙ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባለፉት አምስት ዓመታት ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም ከሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ተግዳሮቶች ገጥመውታል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ስራ እድል ፈጠራና የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚሉ ሶስት ግቦች ቢኖሩትም በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። በቅርቡ የተጀመረው አጠቃላይ አገራዊ የፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ የለውጥ ሥራ ግን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ፍሰት እምርታ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። እስካሁንም ቴሌኮምን ጨምሮ በሌሎች ወደግል ሊዛወሩ በታቀዱ ፕሮጀክቶች ላይ የታየው ፍላጎቶች ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ እምርታ እንዲኖረው ያስችላል ነው ያሉት። በተለይ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ በከፍተኛ የውጭ ባለሀብቶች ዘንድ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከሰሞኑ የ2011 በጀት ዓመት የመንግስትን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ወደግል የማዛወር ተግባሩ የተፈለገውን ዓላማ እንዲያመጣ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ነበር። የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማዛወር ሥራው የሚከናወነው በቅደም ተከትል መሆኑን ጠቅሰው በመጀመሪያ ዙር ኢትዮ ቴሌኮምና የስኳር ፕሮጀክቶች፣ በሁለተኛ ዙር የሃይል ማመንጫዎች፣ የባቡርና የሎጀስቲክስ ፕሮጀቶች በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚሆኑ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ዋና ስራ ቢሆንም መዋለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ውጤታማ ስራዎች እንዲያከናውኑ መንከባከብና ከሰላምና መረጋጋት ጋር የተያያዙ ስራዎች መስራት እንደሚገባ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንተነህ ገልጸዋል። በተለይም ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ሰላምን የማረጋገጥና ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ከኤሌክትሪክ፣ ከኢንተርኔትና ከጉምሩክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የድጋፍና ክትትል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። ስትራቴጂክ ዕቅዱ ወደተግባር ሲገባ ፕሮጀክቶቹ በኤክስፖርት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በምርታማነት መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር ትስስር ተፈጥሮላቸው የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ተስፋ መኖሩን ገልጸዋል። ለበርካታ ዓመታት ትኩረት ከነበረው የጥሬ ምርቶች ኤክስፖርት ወደኢንዱስትሪና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ኤክስፖርት መጠን ለማሻሻል በኢንዱስትሪ ግብዓቶች እሴት ሰንሰለት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም