በህንድ በሙቀት መጨመር ምክኒያት የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ

53
ሰኔ 27/2011 /ኢዜአ/በህንድ በተያዘው የበጋ ወቅት በተከሰተው ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ምክኒያት በብሃር ግዘት ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ህይወት አለፈ። ይህን ተከትሎ በማሳቹሰትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሃይድሮሎጅና የአየር ንብረት ለውጥ  ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤልፋቲህ ኢልታሂር በሰጡት አስተያየት በህንድ በቀጣይ ጊዜያት የሙቀት መጠኑ አሁን ከተከሰተው በበለጠ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችልና ለህይወትም አስጊ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት በህንድ የሞንሱን ዝናብ በሚታይበት በመጋቢትና ሃምሌ ወራት መካከል አንዴ ሲከሰት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ሁኔታዎች እየተቀያየሩ የሙቀት መጠኑ እየበዛ፣ ድግግሞሹ ደግሞ እየጨመረ እንደመጣ ተገልጿል። የማሳቹሰትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ደግሞ ምንም እንኳ በዓለም በብዙ አካባቢዎች የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ አበረታች ጅምሮች ቢታይም በህንድ  በአንዳንድ ስፍራዎች ግን በተቃራኒው የሙቀት መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ በመምጣቱ ለመኖር አዳጋች ሁኔታዎችን ፈጠሯል ብለዋል። የአገሪቱ መንግስትም ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ የአየር ፀባዩ ከተለመደው በላይ የ4.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ጭማሪ ማሳየቱን በማረጋገጥ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአገሪቱ ዋና ከተማ ኒው ደሊሂ አካባቢም ላለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ወደ 45 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ  እንዳለ ተገልጿል። በዋና ከተማዋ በስተ-ምዕራብ አቅጣጫ የሙቀት መጠኑ  ጨምሮ በታሪክ ከፍተኛው 48 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሆኖ ባለፈው ሰኔ ወር ተመዝግቧል፡፡ በህንድ ደሃ ግዛት እየተባለች በምትጠራው ብሃር ውስጥ በሙቀት መጨመር ምክኒያት የ100 ሰዎችን ህይዎት ማለፍ ተከትሎ በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና  የስልጠና ማዕከላት ተዘግተዋል። አንድ ኢንተር-ገቨርመንታል ፓናል ክላይሜት ቸንጅ የተባለ ድርጅትም ህንድ ወደ ፊት ከፍተኛ የአየር ንብረት ቀውስ ከሚከሰትባቸውና ለመኖር አስቸጋሪ ከሚሆኑ የአለም አካባቢዎች  መካከል አንዷ እንደምትሆን ትንባያውን ማስቀመጡን የዘገበው ሲኤንኤን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም