ውሳኔው በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የነበረውን ወንድማዊ ግንኙነት ያጠናክራል - የጦርነቱ ተሳታፊዎች

67
ደብረ ብርሃን ሰኔ 3/ 2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ  ኮሚቴ በኢትዮ­ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ያሳለፈው ውሰኔ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የነበረውን ወንድማዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክር በጦርነቱ የተሳተፉ የቀድሞ ወታደሮች ገለፁ፡፡ በወቅቱ በሲቪል ወታደሩን ለመደገፍ ዘምተው የ107ኛ ኮር አባል የነበሩት አቶ ሳሙኤል አለነ ለኢዜአ እንደገለጡት በኢትዮ- ኤርትራ መካከል ተፍጥሮ በነበረው የድንበር ግጭት የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ወደ ሰራዊቱ ተቀላቅለው በባድመ ግንባር እንደነበሩ አስታውሰዋል። ጦርነቱ እልባት ቢያገኝም ለግጭት ምክንያት የሆነው አብይ ጉዳይ ሳይፈታ ለ18 ዓመታት በመቆየቱ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም በማምጣት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ በአተገባበሩ ዙሪያ ግን ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ የ31ኛ ክፍለ ጦር 33ኛ ሻምበል አመራር የነበሩት መቶ አለቃ ጭንቅል ጉችማ በበኩላቸው የኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈው አመራጭ የሌለው ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል። ''በዚያን ጊዜ የነበረው ጦርነት አሁን ላይ ሆኜ ስመለከተው አልሸነፍም ባይነት የደረሰ ግጭት እንጂ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ጥላቻ አልነበረም'' ብለዋል፡፡ በመሆኑም የአልርጀርሱን ስምምነት ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ያቀረበው ጥሪ ተገቢ መሆኑን ገልጠዋል። በደም  ትስስር ያላቸውን ሁለቱን ህዝቦች በማቀራረብና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ሀገራቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ውሳኔው ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም