በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት ሊሰራ ይገባል ተባለ

195
ሰኔ 27/2011 በኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (የሮቦት ቴክኖሊጂ) ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ አውደ ጥናት ማካሄድ ጀምሯል። በአውደ ጥናቱ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ላይ እየተሳተፉ ነው። ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?፣ በኢትዮጵያ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ጥቅም እንዲያስገኝ ከመንግሥትና ከምሁራን ምን ይጠበቃል? የሚሉት የአውደ ጥናቱ የትኩረት ነጥቦች ናቸው። ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስንስ ከ50 ዓመታት ወዲህ መነገር ቢጀምርም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ሳምሰንግ፣ ማይኮሮሶፍት፣ ፌስቡክ የመሳሰሉ ኩባንያዎች መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስለ ማመዛዘን ዕውቀት፣ ዕቅድ፣ መማርና ቋንቋ ፅንሰ ሀሳባዊ ምንነት በሳይንሳዊ ትንታኔ ያቀርባል። ቻይና መጀመሪያ ቴክኖሊጂውን ኮፒ ታደርግ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የረሷን መፍጠር ጀምራለች። እስራኤልም በተመሳሳይ በስፋት በመጠቀም ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላት ደረጃ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ወደ ኋላ ቀርታለች። አገራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ  እየሆኑ መሆኑን ጠቅሰው አርትሬፊሻል ኢንተለጀንስ ዋነኛ የዕድገት መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን ያነሳሉ። ዘርፉ ለአገር እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማጉላት መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው በትምህርት ቤቶችም ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት የአርቴሺፋል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል ተቋቁሟል ያሉት ፕሮፌሰሩ በማዕከሉ ውስጥ የምርምርና ትምህርትን የመሳሰሉ አገልግሎቶች በተቀናጀ መንገድ መስጠት የሚያስችል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአገሪቷ በአግባቡ በመተግበር መጠቀም እንዲቻል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ባይ ናቸው። የተለያዩ አገራት ዘርፉን ከፍተኛ በጀት እየመደቡ እያሳደጉት መሆኑን ጠቁመው ከኢኮኖሚ እድገት ባለፈ ለአገር መከላከያና ደህንነት በስፋት እየተጠቀሙበት ነው ሲሉም አክለዋል። በጤና፣ ትምህርትና ኢንዱስትሪዎች ላይ በመስራት ከመስኩ የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል። በኢትዮጵያ አዲስ ከመሆኑ አኳያ የተማረ የሰው ኃይልና የካፒታል እጥረት በመኖሩ ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል እንዳያድግ ማነቆ መሆኑንም አንስተዋል። የአይኮ ግላብ መስራችና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት አሰፋ በግብርና፣ ትራንስፖርት፣ የኮሚኒኬሽን ሥራዎችን በማቃለል በኩል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። ወደ ዘርፉ የሚገቡ ኩባንያዎችን በመንግሥት በኩል ማበረታቻ አለመኖሩን ገልፆ በቀጣይም ትኩረት እንዲቸረው ጠይቋል። የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሳይንሳዊ እውቀትን በግብዓትነት በመጠቀም የሚንቀሳቀሱና እንደ ሰው አመዛዝነው ውሳኔ የሚሰጡ እንዲሁም ሰውን ተክተው ወይም ጎን ለጎን የተለያዩ ተግባራትን የሚከውኑ ሜካኒካዊና ኤሌክትሮኒካዊ  ሮቦቶችን የሚያጠና ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ ቁስ አካላዊ ሮቦቶችን ብቻ ሳይሆን መረጃን የሚያቀነባብሩ ብልህ የኮምቲውተር ሲስተሞችንም ያጠቃልላል፡፡ ሮቦቲክስ የሚባለው ደግሞ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያገኘውን የውስብስብ ፅንሰ ሀሳቦች ምንነትና ሌሎች ተጓዳኝ የምህንድስና ዕውቀት በመጨመር ለተለያዩ ጥቅም የሚውሉ ሮቦቶችን የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም