የህግ የበላይነትን ለማስከበር ህብረተሰቡ የድርሻው ሊወጣ ይገባል ተባለ

53
ሰኔ 27/2011 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችና አለመግባባቶችን ለመግታትና የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ አብሮ የሚያኖሩና አንድ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው ልዩነት ላይ ትኩረት እየተደረገ መምጣቱ በአገር አንድነት ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን በከተማዋ የአራት ኪሎ አካባቢ  ነዋሪ አቶ አለማየሁ ተፈሪ ይገልጻሉ። “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባሉ ፣ መተሳሰቡ ፣ መተባበሩና ፍቅሩ” ከፍተኛ አደጋ እየተጋረጠበት እንደሆነም ነው ያብራሩት። የችግር አፈታት ዘዴዎች ፣ መተሳሰብ እና ልዩነትን አጥብቦ አንድነትን የሚያጠናክሩ ባህሎች ሙሉ በሙሉ ከመጥፋታቸው በፊት መንግስትም ሆነ ሕብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ነው የመከሩት። ወጣቱን ትውልድ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከመላክ ባሻገር ከቀደመው ትውልድ የተወረሱ የአብሮነትና የመተሳሰብ ባህልን ማስተማር የህብረተሰቡ ድርሻ መሆኑንም  አቶ አለማየሁ ጠቅሰዋል። “ሁሉም በምን አገባኝነት የራሱ አቅጣጫ ብቻ ይዞ የሚጓዝ ከሆነ የኢትዮጵያ አንድነት ውሃ በልቶት ይቀራል”  ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ቀደም ሲል የነበረው የራስም ሆነ የጎረቤት ልጅ ሲያጠፋ የማረም ልምድ እየጠፋ መምጣቱና ወጣቱ ትውልድ ወደ ጥፋት መንገድ ሲያመራ ዝምታን መምረጥ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በማውገዝ እና በማስቆም የህግ የበላይነትን በማስከበር ለጋራ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ጠቅሰው፤ መንግስትም የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው “ብሄር ውስጥ ተደብቆ ልዩነት ማቀንቀን” የአገር አንድነት ከመናድ ውጪ ማንንም አይጠቅምም ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሃይለማርያም ሃይሉ ናቸው፡፡ የአንዲት አገር ሰላም ከተናጋ በሰላም ወጥቶ መመለስና ሰርቶ መኖር አዳጋች በመሆኑ ወንጀልን በመከላከል ለሰላም መረጋገጥና  አገራዊ አንድነት  በጋራ  መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ “እንደቀድሞው አንድነታችንን አጠናክረን፣ ተቻችለንና ተከባብረን አገሪቷን ለማሳደግ አብረን ከሰራን ኢትዮጵያ ከኛ አልፋ ለሌላም ትተርፋለች” ያሉት አቶ ሃይለማርያም እርስ በእርስ በመተባበርና በመደጋገፍ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባም ነው የገለጹት። አገሪቷ ወደ እርስበርስ ግጭት  ገብታ የመበታተን አደጋ እንዳይገጥማት ከህብረተሰቡ  ጥረት ባሻገር  መንግስትም ህግን በማስከበር ሂደት ትእግስቱ ገደብ ሊኖረው እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከዘመናዊ የመንግስት አሰራር ጋር አቀናጅቶ ማስኬድ ባለመቻሉ ችግሮች እንዲባባሱ ማድረጉን ያብራሩት ሌላው አስተያት ሰጪ አቶ እያሱ ወልደስላሴ ፤  ከየትኛውም ብሄር የሚመጣ ፅንፈኛ የራሱን የስልጣን ጥማት እንጂ የህዝብ ጥቅምና ኢትዮጵያን እንደማይወክልም ነው የገለጹት። ይህ አካሄድ “ያለው ሃብትና ጉልበት በምን መንገድ መጠቀምና ማሳደግ እንዳለበት ከመንገር ይልቅ ይሄ ብሄር ላንተ አደጋ ነው እያለ ሥራ ሰርቶ እንዳያድግ፤ ወደ ጦርነትና ጭፍን ጥላቻ በመክተት የአገሪቷን ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል ያደርጋል’’  በማለትም ነው የጠቀሱት፡፡ “ቋንቋችን በራሱ ባንድም በሌላ የተወራረሰ ነው፤ ይሄ አንድነታችንን ነው የሚያሳየው” ያሉት  አቶ እያሱ  አፋርኛ፣ ሳሆኛ፣ ትግርኛና አማርኛ መናገር እንደሚችሉና ሌሎች ቋንቋዎችንም በመማር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፤  ቋንቋ መግባቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ መሆን እንደሌለበት ይመክራሉ። በየአካባቢው ያሉ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች  ህብረተሰቡን በማስተባበር የህግ የበላይነት እንዲከበር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው መንግስትም መስተካከል ያለባቸውን ህጎች በማሻሻል  የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም