ምክር ቤቱ በአሰሪና ሰራተኛ መካካል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል የተባለውን የማሻሻያ አዋጅ አጸደቀ

76
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2011  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እና መመሪያ ላይ የሚያጋጥሙ የአፈጻጸም ችግሮችን ይፈታል የተባለ የማሻሻያ አዋጅ ዛሬ አፀደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 47ኛ መደበኛና 9ኛ ልዩ ስብሰባው ላይ ነው አዋጁን ያጸደቀው። የምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አዋጁ  በአሰራና ሰራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያግዛል። አዋጁ አገሪቱ እያስመዘገበች ካለችው ዕድገትና ከተነደፉ የልማት ፖሊሲዎች ጋር እንዲጣጣምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመጣው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እንዲሄድ ተደርጎ መሻሻሉን ገልፀዋል። የተሻሻለው አዋጅም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን ሰላማዊ በማድረግ ሰራተኛው ሙሉ አቅሙን ምርትና ምርታማነት ላይ በማዋል ትርፋማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል። ከነባሩ አዋጅ ላይ ስድስት የሚሆኑ አንቀጾች የተሻሻሉ ሲሆን አብዛኞቹ ከአካል ጉዳተኞችና ከሴቶች ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ ናቸው። አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በተሻሻሉት አንቀፆች ውስጥ በነፍሰ ጡር ሴት የወሊድ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ቀድሞ በነበረው አዋጅ ነፍሰ ጡር ሴት ከምትወልድበት ቀን ቀደም ብሎ 30 የስራ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድና ከወለደች በኋላ ደግሞ  60 የስራ ቀናት የድህረ ወሊድ ፍቃድ'  ይሰጣት ነበር ፤ ሆኖም በተሻሻለው አዋጅ ይህንን በተመለከተ የተቀመጠው አንቀፅ '30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ እንዲሁም 90 ተከታታይ ቀናት የድህረ ወሊድ ፍቃድ ታገኛለች' የሚል ነው። አባላቱም በተሻሻለው አዋጅ 90 ተከታታይ ቀናት የሚለው 'የስራ ቀናት' በሚል እንዲለወጥ በመጠየቅ ተከራክረዋል። ሆኖም የምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በሰጡት ምላሽ እንዲካተት የተጠየቀው አንቀፅ ፋብሪካዎችና የመንግስት ያልሆኑ ተቋማት ቅዳሜና እሁድ የባዕል ቀናትም ስራ ስለሚሰሩ በዚህ ተቋም የሚሰሩ ሴቶች እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሰለሚያደግና ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ሲባል 'ለ90 ተከታታይ ቀናት' የሚለው ሀረግ ተወስዷል ብለዋል። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የተጨማሪ እሴት ታክስን ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች አስተዳዳር ረቂቅ ደንብን ዛሬ አጽድቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም