የአየርላንድ መንግስት ለምርጫ ማስፈፀሚያ አቅም ግንባታ የሚውል ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

76
ሰኔ 27/2011የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ምርጫና የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባራትን አቅም ለማሳደግ ለሚከናወኑ ሥራዎች የሚውል ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ሰጠ። ድጋፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አቅምን ለማሳደግ፣ ግልፅ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ተቋም እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ተብሏል። የገንዘብ ድጋፍ  ስምምነቱን  በኢትዮጵያ የአይርላንድ አምባሳደር ሚስ ሶንጃ ሃይላንድ እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም /ዩኤንዲፒ/ ተወካይ ቱራን ሳህላህ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ፈርመዋል። በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ ተገኝተዋል። ወይዘሮ ብዙወርቅ ለኢዜአ እንደገለፁት፤የአየር ላንድ መንግስት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ነፃ እና ግጭት አልባ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በኢትዮጵያ እንዲካሂድ የተጀመረውን ጥረት ያግዛል። በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት እንዲካሄድ፣ ወጣቶች እና ሴቶች በምርጫ ሂደት እንዲሳተፉ፣ ለማስቻል ለሚከናወኑ ተግባራትም አስተዋፆ ይኖረዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ የአየር ላንድ አምባሳደር ሚስ ሶንጃ ሃይላንድ በበኩላቸው ድጋፉ ዴሞክራሲን ለማጎልበትና የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል። በዚህ መሰረትም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወኪል ለሆነው የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ገንዘቡን ማስረከባቸውን አክለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም /ዩኤንዲፒ/ ተወካይ ቱራን ሳህላህ፤ የአየር ላንድ መንግስት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ምርጫ ግልፅ፣ ውጤታማና አሳታፊ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሆነም አብራርተዋል። ለዚህ ስራ የአየር ላንድ መንግስትም ሆነ ሌሎች አጋር አካላት እያደረጉት ላሉት ድጋፍ ምስጋና ችረው ኢትዮጵያ እያከናወነች ካለው የለውጥ ሂደት አኳያ መጪው ምርጫ ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ምርጫ የማስፈጸምአቅምን ለማጠናከር የሚያስችል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም