በአማራ ክልል ትራክተሮችን በመጠቀም 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር እየተሸፈነ ነው

49
ባህር ዳር ሰኔ 27 / 2011 በአማራ ክልል በ2011/12 የምርት ዘመን ትራክተሮችን በመጠቀም 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የእርሻ መካናይዜሽን ባለሙያ አቶ ሃብተማርያም ዜና  ለኢዜአ እንደተናገሩት የመኽር ወቅት እርሻ በክልሉ ስድስት ዞኖች 697 ዘመናዊ ትራክተሮች የእርሻ ሥራው እየተከናወነ ነው። በዚህም ለትራክተር እርሻ አመቺነት ባላቸው በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና አዊ ዞኖች ሥራው እየተካሄደ  ይገኛል ብለዋል። ሥራው እየተከናወነ ያለውም በዩኒየኖች፣ በኅብረት ሥራ ማህበራትና ባለሃብቶች በቀረቡ  አማካኝነት መሆኑንም ባለሙያው ገልጸዋል። እስካሁን በተከናወነው እንቅስቃሴም የ36 ሺህ አርሶ አደሮች 50 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በትራክተር መታረሱን አስረድተዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማረስ ለግብርና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የገለጹት ባለሙያው፣ወቅትን ጠብቆ የእርሻ ሥራው ከተከናወነም የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የሰብል ምርታማነት እንዲያድግ፣ ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ ተባይን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል። ቢሮው በተጨማሪም ጥቁር አፈርን ለማጠንፈፍ ከ10 ሺህ የተሻሻለ የእርሻ ማረሻ መሣሪያዎች መሰራጨታቸውን አቶ ሃብተማርያም ተናግረዋል። እንዲሁም ምርትን ለማሳደግ የሚያግዙ ከ1 ሺህ 480 የሚበልጡ ጤፍን በመሥመር መዝሪያ መሣሪያዎች መከፋፈላቸውንም ጠቁመዋል። በአዊ ዞን የሚገሸው የአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረትሥራ ማህበር ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ወርቄ  አርሶ አደሩ የዘመናዊ እርሻ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ  እንዲሆን በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ አምስት የእርሻ ትራክተሮችን ገዝቶ  አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ክፍያ የእርሻ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በትራክተር ማረስ የአፈር ለምነት ከማሻሻል በተጨማሪ በሄክታር እስከ አምስት ኩንታል ተጨማሪ ምርት ያስገኛል ያሉት በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ ማር ወለድ ቀበሌ አርሶ አደር ባዩ ተጃረ ናቸው። በዚህ ዓመት ለስንዴ ልማት የሚሆን አንድ ሄክታር መሬት በሁለት ሺህ ብር ሂሳብ በትራክተር ማሳረሳቸውን ገልጸዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቸኮል ሁሉቃ በበኩላቸው በየሁለት ዓመቱ የእርሻ መሬታቸውን በትራክተር እንደሚያሳርሱ ተናግረዋል። በትራክተር ማሳረስ መሬቱ ለጎርፍና ለነፋስ እንዳይጋለጥና የአፈር ለምነት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል። በክልሉ በ2010/11 ምርት ዘመን ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በትራክተር ታርሶ መልማቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም