የኦዲት ግኝት የታየባቸው ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበት የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

245
ሰኔ 26 / 2011 የኦዲት ግኝት የታየባቸው ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበት የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፍ እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በሀገር ሃብትና ንብረት ላይ የሚያደርሱት ብክነት ከፍተኛ በመሆኑ ምክር ቤቱ የቀጣዩን ዓመት በጀት ለማጽደቅ መቸገሩ ተገልጿል። በኢትዮጵያ ኦዲት የሚደረጉ ባለበጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኅብረተሰቡ ጋር ባደረገው ውይይትና የመስክ ምልክታ ከ176 የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ነጻ ሆነው የተገኙት 25ቱ ብቻ ናቸው። የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት ትብብር ፎረም ጋር ውይይት አድርጓል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ዩሱፍ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የሚታይባቸው የኦዲት ግኝት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በዚህም በሃገሪቷ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ የሚውለውና የሚባክነው ሃብት ከፍተኛ መሆኑ በፋይናንስ ህጋዊነትና በክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ተረጋግጧል ብለዋል። የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ችግሮችን በወቅቱ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ከማስተካከል ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱንም ጠቁመዋል። የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ማስተካከያ እንዲደረግ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው በቀጣዩ ስራ ላይም እምነት በማጣቱ የአስፈጻሚው የበላይ አካል የሆኑትን የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ለማነጋገር በውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 31/2011 ስምምነት ላይ መድረሱን አመልክተዋል። የመንግስት ግዥና ፋይናንስ ስርዓት ሳይከተል የሚፈጸም ግዥና ክፍያ፤ ስራ ለለቀቀ ሰው ደመወዝ መክፈል እና መሰል የጥፋት ተግባራት ተገቢ እርምጃ አለመውሰድ በስፋት ይታያል ብለዋል። በተጨማሪም መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ በህጉ መሰረት አለመሰብሰብ፣ ከህግ ውጭ ክፍያ መፈጸም፣ የመንግስት ንብረት በአግባቡ አለመያዝ፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ሌሎችም የፋይናንስ አጠቃቀም ችግሮች የውሳኔ ሃሳቡን ለማሳለፍ አስገድደዋል ብለዋል። ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ የሚያደርሱት ብክነት ከፍተኛ ስለሆነም ምክር ቤቱ የቀጣዩን በጀት ለማጽደቅ ተቸግሯል ብለዋል። በመሆኑም የኦዲት ግኝት የታየባቸው ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል። በዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኦዲት ግኝቱ ተለይቶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተልኮ ምርምራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የኦዲት ግኝቶቹ እየተለዩ አስተዳደራዊ መፍትሄ ይወሰዳል፤ የህግና የአሰራር ማሻሻያ ይደረጋል፤ ለህግ የሚቀርቡትም ለህግ ይቀርባሉ ነው ያሉት። በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክተር አቶ ተረፈ አሰፋ የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት ላይ ምርመራ መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንደ ግኝቶቹ አይነትና መጠን የፍትሃብሄርና የወንጀል ክስ ለመመስረትም መረጃዎችን በማጣራት ላይ መሆናቸውም ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም