እየተገነቡ ያሉ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባሪያ ፓርኮች አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶችን እንዲያመርት የሚያበረታቱ ናቸው-ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

71
ሰኔ 2/2020 እየተገነቡ ያሉ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶችን እንዲያመርት የሚያበረታቱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በመላ ሀገሪቱ 17 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች የልማት ኮሪደር የተለየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በትግራይ (ባዕከር)፣ በአማራ (ቡሬ)፣ በኦሮሚያ (ቡልቡላ)ና በደቡብ ክልል (ይርጋለም) አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ግንባታ ተጀምሯል፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ አሰፋ ተስፋዬ እንደገለፁት ፓርኮቹ  የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርቶች በግብአትነት የሚጠቀሙና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግርና የበጀት እጥረት በፓርኮቹ ግንባታ ላይ መጓተት ማስከተሉን ገልጸው አሁን በዘላቂ ልማት ግቦች በጀት ተመድቦላቸው ግንባታቸው በመከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከግንባታው በተጓዳኝ ለፓርኮቹ ግብዓት የሚያቀርቡ ማህበራትም ከወዲሁ እየተደራጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በፓርኮቹ አካባቢ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርት ማሰባሰቢያ ማእከላትን በስፋት ለመገንባትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ተስፋዬ ጨፋና እንዳሉት ፓርኮቹ በአርሶ አደሩ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶችን እንዲያመርት እና ገበያ ተኮር ግብርናው  እንዲስፋፋ  የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ነው ያብራሩት፡፡ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሀገሪቱ ካላት እምቅ የግብርና ሃብት አንፃር የተሻለ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በፓርኮቹ ገብተው የሚያለሙ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንዳሉት አስቀድሞ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና የፓርኮቹን ተወዳዳሪነት በዘላቂነት ለማስቀጠል የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በአጭር ጊዜ እውን ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለአራቱ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ግንባታ 30 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ግንባታቸውን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ (አማራ ክልል)፡-
  • የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በ250 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል፣
  • ለግንባታው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል.
  • ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ600 ሺህ አርሶ አደሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡
ይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ (ደቡብ ክልል)፡-
  • የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በ295 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል፣
  • በግንባታው ሂደት ለ821 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል፣
  • ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ400 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡
ባዕከር የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ (ትግራይ)፡-
  • ግንባታው በ258 ሄክታር መሬት ላይ እየተከናወነ ነው፣
  • ለግንባታው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፣
  • ፓርኩ ሲጠናቀቅ ለ300 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡
ቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርክ፡-
  • በ263 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል፤
  • ለግንባታው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም