የሜታ ሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች ኦነግ ሸኔን በማውገዝ ሰልፍ ወጡ

103
አምቦ ሰኔ 25/2011በምዕራብ ሸዋ ዞን የሜታ ሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች ኦነግ ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ቡድን በማውገዝ ዛሬ ሰልፍ ወጡ፡፡ ሰልፈኞቹ  በሜታ ሮቢ ከተማ ታጣቂው ቡድን በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ እንደሚያወግዙ በያዟቸውና ባሰሟቸው መፈክሮቻቸው ገልጸዋል። እነዚህ 5ሺህ የሚደርሱት ሰልፈኞች ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት እታገላለሁ የሚለው  ቡድን ሕዝቡን እንደማይወክል አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት  የሕዝቡን ሰላም የሚያውከውን ቡድን ለይቶ እርምጃ  በመውሰድ የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም ከመንግሥት ጎን በመቆም ሕዝብ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን እንደሚታገሉም አረጋግጠዋል። ከዚህም ሌላ ሰልፈኞቹ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መሪዎችና በጄኔራል መኮንኖች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘዋል። ድርጊቱ በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የታቃጣ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ተናግረዋል። በከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት እጃቸው አለበት የተባሉ ቡድኖችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በየአካባቢው እያደረጋቸው ባሉት ሰላማዊ ሰልፎች ለክልሉ ሕዝብ ነፃነት ቆሜያለሁ የሚለውን ቡድን እያወገዘ ነው። የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦነግ)የትጥቅ ትግል ያቆመበትን ስምምነት ከመንግሥት ጋር በማድረግ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከአሥመራ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም