ኢዜአን መልሶ ለማቋቋም የወጣን አዋጅ ለማስፈጸም የቀረበ ረቂቅ ደንብ ጸደቀ

58

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅን ለማስፈጸም የቀረበለትን ረቂቅ ደንብ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን መልሶ ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም የቀረበን ረቂቅ ደንብ ጨምሮ ሰባት አዋጆችን አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መልሶ ለማቋቋም የወጣን አዋጅ ለማስፈጸም የቀረበው ረቂቅ ደንብ ኢዜአ የአገሪቷን ባህሎች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለአገር ውስጥና ለውጭ በማስተዋወቅ የአገር ገጽታ ግንባታ ስራውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ያስችለዋል ተብሏል።

ረቂቅ ደንቡ ከዚህ ባለፈ ዜና አገልግሎቱ መስራት የሚጠበቅበትን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለመፈጸም የሚያስችለው ከመንግስት ከሚመደብለት በጀት ባለፈ በራሱ ገቢ ሊያመነጭ እንደሚገባ በአዋጁ የተደነገገውን  ከምንና በምን አይነት ሁኔታ ገቢ ማስገኛ ምንጮችን እንደሚፈጥር ለይቶ ማመልከቱ ነው የተብራራው።

የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ ደንቡን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ  በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ ና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም ከህግ ፍትህና ዴሞራሲ ጉዳዮች የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብንም መርምሮና መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ነጥቦች አሻሽሎ ረቂቅ አዋጁን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፣ በኢትዮጵያ መንግስትና በእስራኤል መንግስት መካከል በጉምሩክ ጉዳዮች ላይ የተደረገን ስምምነት፣ በግብርና እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ለመተባበር የተደረገውን ስምምነትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የዶክተር ዳንኤል በቀለን ሹመትም አጽድቋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም በፌዴራሊዝሙ የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት (Intergovernmental Relations(IGR) ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም