በዩኒቨርሲቲዎች ግልጽ የፋይናንስ አሰራር ስርዓት አለመዘርጋቱ ለከፍተኛ የኦዲት ግኝት አጋልጧቸዋል ተባለ

61
አዲስ አበባ  ሰኔ 25/2011  ዩኒቨርሲቲዎች ስራቸውን የሚያከናውኑበት ግልጽ የፋይናንስ አሰራር ስርዓት አለመዘርጋቱ ለከፍተኛ የኦዲት ግኝት አጋልጧቸው እንደነበርር የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ። በኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት ኦዲት ከተደረጉ 174 የመንግስት ተቋማት መካከል 129ኙ የኦዲት ግኝት ታይቶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል 60ዎቹ ተቋማት ከፍተኛ የኦዲት ችግር የታየባቸው እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውም ተገልጿል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና ሌሎች ስራዎችን ያከናውናሉ። የምርምር፤ የስራ እድል ፈጠራ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ለሚያወጡት ወጭ ደግሞ ግልጽ አሰራር አልተቀመጠም ብለዋል። የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የትርፍ ሰዓት ስራ ሲሰሩና ጥናትና ምርምር ሲያካሂዱ የሚያስፈልጋቸው ክፍያ ተመን ስላልነበረው ክፍያው በዘፈቀደ ይፈጸም እንደነበርም አልሸሸጉም። በዚህም ዋና ኦዲተር መመሪያ አሰራር በሌላቸው የክፍያ ስርዓቶች የሚያገኘውን የፋይናንስ ፍሰት የኦዲት ግኝት ነው ለማለት መገደዱን ገልጸዋል። እነዚህ የኦዲት ግኝት ችግሮቹ ሲከሰቱ የቆዩትም በዩኒቨርሲቲዎች ጥፋት ብቻ ሳይሆን ሳይሆን በመንግስት የአሰራር ክፍተት በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የፋይናንስ አሰራር ስረዓት ተዘርግቷል ብለዋል። በመሆኑም አሁን የዩኒቨርሲቲዎች ለትርፍ ሰዓት ክፍያን ጨምሮ ሌሎች ተመን ላልወጣላቸው ክፍያዎች የክፍያ ተመን እንዲወጣላቸው ተደርጓል ብለዋል። በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚከሰተው የኦዲት ግኝት ለሚሲዮኖች የፋይናንስና ግዥ የሚመራበት መመሪያን በማውጣት ወጥ አሰራር እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ የኦዲት ግኝት የታየባቸው ተቋማትን በመመሪያው መሰረት ተጠያቂ ለማድረግ ግኝቶች እየተለዩ መሆኑንም ገልጸዋል። በ2009 በጀት ዓመት ከፍተኛ የኦዲት ግኝት ከታየባቸው 61 ተቋማት 45ቱ ዘንድሮም ባሉበት መቀጠላቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እነዚህን ተጠያቂ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መስጠት መጀመራቸውንና የጥፋቱ አይነትና መጠን እየተለየ ከገንዘብ እስከ እስራት ቅጣት እንደሚተላለፍባቸውም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ በ 2008 ዓመተ ምህረት የወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ የሁሉም ተቋማት የኦዲት ግኝት በአይነትና በመጠን እየተለየ መሆኑን አስረድተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም