በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 12 ሰዎች በነጻ ተሰናበቱ

80
አሶሳሰኔ 25/2011የቤንሻጉል ጉምዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ 12 ሰዎችን በነጻ አሰናበተ። በክልሉ በ2004 ዓ.ም በአራት የክልሉ ወረዳዎች የተካሄዱ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ስራቸው ከጨረታ እስከ ግንባታ  ጥራቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ከፍተኛ ሀብት ባክኗል በሚል ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ማስረጃ ሲያጣራ ቆይቷል። የፖሊሲን ማስረጃ መሰረት በማድረግ የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሚያዝያ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በወንጀሉ የተጠረጠሩ 12ቱን ግለሰቦች ሲያከራክር ቆይቷል። ከተጠርጣሪዎቹ አስሩ የክልሉ የግብርና ቢሮ ሠራተኛ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ስራ ያከናወኑ ተቋራጮች ባለቤቶች ናቸው። የዞኑ ፍርድ ቤት ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት “የመስኖ ፕሮጀክቶቹየተካሄዱት በፌዴራል መንግስት በተመደበ በጀት በመሆኑ ጉዳዩን መመልከት ያለበት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው’’ በሚል ተጠርጣሪዎቹን በነጻ  አሰናብቶ ነበር። በወቅቱም ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩ የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች “ በተጠርጣሪዎች ላይ በጊዜ ቀጠሮ ይደረግ የነበረው ክርክር የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ስልጣን ሳይኖረው ያደረገው ክርክር በመሆኑ ውድቅ አድርገነዋል’’  ማለታቸው ይታወሳል። ‘’የሚመለከተው አካል ጉዳዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ’’ ሲሉም ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር። የከልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቅ ጉዳዩ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲታይና ተጠርጣሪዎቹም በእስር እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲልከማረሚያ ቤት እንዳይወጡ የተጣለውን እግድ አንስቶ በነፃ አሰናብቷል። የክልሉ ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄዳው 4ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ከዚሁ የከባድ ሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥያቄ የቀድሞው የምክር ቤቱን ዋና አፈጉኤ የነበሩትን የአቶ ሙለታ ወምበርን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም