በሞት የተለዩንን የጦር መሪዎች አደራ ወጣቱ ማስቀጠል አለበት…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

99
ሰኔ 24/2011 በሞት የተለዩንን የጦር መሪዎች አደራ ወጣቱ ማስቀጠል እንዳለበት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። የጄኔራል አብርሃ ወልደማርያም/ኳርተር/ የቀብር ሰነ-ስርዓት በመቀሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተፈፅሟል። በስነ-ስርዓቱ ላይ ዶክተር ደብረጽዮን "ጀነራል አብርሃ ለህዝብ ክብር ያበረከተና የማይደበዝዝ ታሪክ የሰራ የጦር መሪ ነበር" በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል። "ከመስዋእት መሸሽ ሳይሆን መስእዋት እስኪመጣ ድረስ ለህዝብ አገልግለህ መሞት ክብር ነው" ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን "ጄኔራል አብርሃ ለዚሁ ተምሳሌት ተጠቃሽ ነው" ብለዋል። የትጥቅ ትግሉ ካፈራቸው ኢትዮጵያዊ ምርጥ ጄኔራሎች አንዱ ስለመሆናቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተው በተሳተፉባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ታሪክ ከመስራት ባለፈ ሃገሪቱ ሰላሟን አስጠብቃ ሕዳሴዋን እንድታስቀጥል ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ ታጋይ እንደነበሩም ተናግረዋል። ጄኔራል አብርሃም ወልደማርያምን ጨምሮ በዚህ ሳምንት በሞት የተለዩንን ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችን አደራ ወጣቱ ትውልድ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። የጀኔራል አብርሃ አስከሬን በሰማእታት ሀውልት በማረፍ የህይወት ታሪክ ከማንበብ በተጨማሪ የፍትሀት ፀሎት በማከናወን የቀብር ስነ-ስርዓቱ በመቀሌ ቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስቲያን ዛሬ የተፈጸመ ሲሆን ለክብራቸውም 12 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። ጀነራል አብርሃ ወልደማርያም ኳርተር በ1971 ዓ.ም ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወታደራዊ ብቃታቸውን በማሳደግ ከተራ ወታደር እስከ ጄኔራል ማእረግ የደረሱ የጦር መሪ እንደነበሩ ከህይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም