የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎችን ልንታገላቸው ይገባል - በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተመራቂ ወላጆች

63
ሰኔ 24/2011የኢትዮጵያን አንድነትና እድገት የማይፈልጉ ኃይሎችን ከመንግስት ጎን በመቆም ልንታገላቸው ይገባል ሲሉ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርአት ላይ የተገኙ ወላጆች ገለፁ። ኢትዮጵያዊያን የመቻቻል፣ የመከባበርና የአንድነት እሴቶቻችንን አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል ሲሉም ወላጆቹ መልእክት አስተላልፈዋል ። ከኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና ልጃቸውን ለማስመረቅ ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ አቶ ኤፍሬም ህንሾ ለኢዜአ እንዳሉት በተዘዋወሩባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የህዝቡ የእንግዳ ተቀባይነተና የመከባበር መንፈስ ጠንካራ መሆኑን ተገንዝበዋል ። “የህዝቦችን አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ ኃይሎችን ከመንግስት ጎን በመቆም ልንታገላቸው ይገባል “ ብለዋል ። መንግስት የህዝቦችን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡን የማረጋጋትና አንድነቱን አጠናክሮ የማስቀጠል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ነው የጠየቁት። “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች በህዝቦች የተፈጠሩ አይደሉም “ያሉት ደግሞ ከአዲስ አበባ የመጡት ወይዘሮ አፀደ ገብረመስቀል ናቸው ። “የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ጥቂት ኃይሎችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ። “ኢትዮጵያዊያን  የቆየ የመከባባር፣ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶቻችንን ልናስቀጥል ይገባል” ያሉት ደግሞ ከጎንደር ከተማ የመጡት አቶ አለማየሁ ኃይሉ ናቸው ። በተለይም ወጣቱ ትውልድ በሐሳብ በመግባባትና በመነጋገር የሀገሪቱን ብሩህ ተስፋ ሊያስቀጥል እንደሚገባ መክረዋል ። በህዝቦች መካከል የመለያየትና የጥላቻ ስሜት ተወግዶ የሀገራዊ እንድነት መንፈስ እንዲጎለብት ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ግለስቦችና የሃይማኖት መሪዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመላክተዋል ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም