የደምቢዶሎ ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው ፕሮጀክት በመጓተቱ ቅሬታ እንዳደረባቸው ነዋሪዎች ገለጹ

72
ነቀምቴ ሰኔ 2/2010 የደምቢዶሎ ከተማን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በ125 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት በመጓተቱ ቅሬታ አሳድሮብናል  ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ። የከተማዋ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ ''በግንባታ ሒደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የነዋሪውን ጥያቄ ለመመለስ  እየጣርኩ ነው'' ብሏል ። በከተማው የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ ምትኬ አማሮ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ከንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የተነሣ ረጅም መንገድ በመጓዝ ለጤና ተሰማሚ ያልሆነ የጉድጓድ ውሃ አንዱን ጀሪካን በ2 ብር ለመግዛት ተገደዋል። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ገዛኸኝ ታዬ በበኩላቸው "አዲሱ ፕሮጀክት ባለመጠናቀቁ  ምክንያት የከተማዋ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከነባሩ አገልገሎት መስጫ  ለማግኘት ከሶስት ሳምንት እስከ አንድ ወር ድረስ መጠበቅ ግዴታ እየሆነበት መጥቷል" ብለዋል ። ''በ15 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ በ2007 ዓም በተጀመረው የውሃ ፕሮጀክት ላይ ተስፋ ጥለን የነበረ ቢሆንም ለአገልግሎት ሳይበቃ 20 ወራት በማስቆጠሩ ችግራችን እየከፋ መጥቷል'' ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል ። በከተማው የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ኡልፊና ተርፋ በሶስት ሳምንት አንድ ጊዜ በወረፋ የሚለቀቀውን የውሃ  አገልግሎት ለነዋሪው ሕዝብ ፈታኝ በመሆኑ የተጀመረው የፕሮጀክት ሥራ ተፋጥኖ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል። የደምቢዶሎ ከተማ  የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ድርጅት የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደበላ በቀለ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ ''ህዝቡ ያነሳው ቅሬታ ተገቢ ነው'' ብለዋል ። በከተማው አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት 10 ሺህ ሰዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ከዓመታት በፊት የተሰራ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የከተማው ሕዝብ ብዛቱ ከ80 ሺህ በላይ በመሆኑ አገልገሎቱን በየቀኑ ማዳረስ አለመቻሉን አስረድተዋል። ያለውን የውሃ አቅርቦት በወረፋ በፍትሃዊነት ለማዳረስ ጥረት ቢደረግም  ሁሉንም የከተማው ክፍል  በዙር ለማዳረስ ከሦስት ሳምንታት በላይ  እየወሰደ መሆኑንም አስታውቀዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት  በተመደበ 125 ሚሊዮን ብር ግንባታው  የተጀመረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በወቅቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት አለመብቃቱም  ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው አቶ ደበላ ተናግረዋል ። '' በፕሮጀክቱ ላይ የዲዛይን ማሻሻያ መደረጉ፣ አዳዲስ ተጨማሪ ስራዎች መካተታቸው እንዲሁም ከውጭ የሚገዙ ዕቃዎች በወቅቱ አለመድረሳቸውና በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍራስ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው'' ብለዋል ። የፕሮጀክቱ አማካሪ ተወካይ አቶ አብርሃም ሁምና በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ ስራ 98 በመቶ መገባደዱንን ገልፀው ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በማጠናቅቅ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል ። የኦሮሚያ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ላሜቻ ፕሮጀክቱ መጓተቱን አምነው፣ በአሁኑወቅት በከተማ ውስጥ የውሃ መስመር ዝርጋት እየተካሄደ በመሆኑና ሥራውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ100 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚዎች ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም